የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሶማሊላንድን እውቅና እንደሚቃወሙ የተናገሩ ሲሆን፤በተመድ የአሜሪካ ምክትል አምባሳደር ታሚ ብሩስም በአሜሪካ ፖሊሲ ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ የለም ብለዋል።
አሜሪካ እስራኤል ከሶማሊያ ተገንጥላ የወጣችውን ሶማሊላንድን እውቅና የመስጠት መብቷን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስብሰባ ላይ የተከላከለች ሲሆን፤ ሁኔታውንም በርካታ ሀገራት ለፍልስጤም መንግስት ከሰጡት እውቅና ጋር አነጻጽራዋለች።
እስራኤል እንደ ማንኛውም ሉዓላዊ ሀገር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የማድረግ እኩል መብት አላት ሲሉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ ምክትል አምባሳደር ታሚ ብሩስ በጸጥታው ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የዚህ ምክር ቤት አባላትን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ለፍልስጤም መንግስት እውቅና ለመስጠት የአንድ ወገን ውሳኔ አስተላልፈዋል፤ ሆኖም ግን የምክር ቤቱን ተቃውሞ ለመግለጽ ምንም ዓይነት አስቸኳይ ስብሰባ አልተጠራም ሲሉ አክለዋል።
ይህ አስተያየት የተሰጠው እስራኤል ዓርብ ዕለት ሶማሊላንድን እንደ ሀገር እውቅና ለመስጠት ማስታወቋን ተከትሎ የተፈጠረውን ዓለም አቀፍ አለመግባባት ለማርገብ ነው።
ይህ የእስራኤል ውሳኔ በአፍሪካ ህብረት፣ በግብፅ እና በአውሮፓ ህብረት ዘንድ ከፍተኛ ትችት አስከትሏል።
ሀገራቸው የፍልስጤምን መንግስት እውቅና የሰጠችው የስሎቬንያዉ አምባሳደር ሳሙኤል ዝቦጋር፤ ዋሽንግተን ያቀረበችውን ንፅፅር ውድቅ አድርገዋል።
ፍልስጤም የማንኛውም ሀገር አካል አይደለችም። እንደ ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት እና ሌሎችም ድርጅቶች ገለጻ በህገ-ወጥ መንገድ የተያዘች ግዛት ነች ብለዋል።
ሶማሊላንድ ግን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል ሀገር አካል በመሆኗ፤ እውቅና መስጠት የተመድን ቻርተር የሚጥስ ነው ሲሉ ዝቦጋር ገልጸዋል።
የጸጥታው ምክር ቤት አባል የሆኑት የሶማሊያ አምባሳደር አቡከር ኦስማን እስራኤል የሰጠችውን እውቅና አውግዘዋል። በርካታ አባል ሀገራትም እስራኤልን በቀጥታ ሳይጠቅሱ ለሶማሊያ የግዛት አንድነት ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
ሶማሊላንድ ከሶማሊያ መገንጠሏን በፈረንጆቹ 1991 ያወጀች ቢሆንም፤ እስራኤል ይፋዊ እውቅና እስከሰጠችበት ጊዜ ድረስ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ለማግኘት ያደረገችው ጥረት ፍሬ ሳያፈራ ቆይቷል።
በአፍሪካ ቀንድ የምትገኘው ሶማሊላንድ ከየመን ማዶ በኤደን ባህረ ሰላጤ አቅራቢያ የምትገኝ በመሆኗ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታዋ ከፍተኛ ነው ሲል ያስነበበዉ ሲ ኤን ኤን ነዉ።
እስከዳር ግርማ
ታህሳስ 21/2018 ዓ.ም
