በሳውዲ የሚመራው ጥምር ጦር በየመን ቀይ ባሕር የወደብ ቀጠና ላይ የአየር ድብደባ ፈጸመ ።

በሳውዲ ዓረቢያ የሚመራው የዓረብ ሀገራት ጥምር ጦር በየመን ቀይ ባሕር ዳርቻ በሚገኝ ስልታዊ የወደብ ቀጠና ላይ የአየር ድብደባ መፈጸሙን አስታወቀ። ጥምረቱ ይህንን እርምጃ የወሰደው ያልተፈቀደ እና ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ጭነት ወደ ሀገሪቱ ሊገባ ነው በሚል ባገኘሁት መረጃ መሠረት ነው ብሏል።

የጥምረቱ ቃል አቀባይ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ድብደባው ያነጣጠረው በሁቲ አማፂያን ቁጥጥር ስር በሚገኝ የወደብ መሠረተ ልማት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ የወደብ ቀጠናው ለሰብአዊ እርዳታ መግቢያነት እንዲያገለግል ቢፈቀድም አማፂያኑ ግን ቦታውን ከውጭ የሚገቡ የላቁ የጦር መሣሪያዎችን ለማከማቸትና ለማሰራጨት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።

ይህ የአየር ጥቃት የተፈጸመው በክልሉ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ ይበልጥ ሊያባብስ ይችላል ተብሎ በሚሰጋበት ወቅት ነው። የሳውዲ መራሹ ጥምረት “ደህንነታችንን የሚፈታተን ማንኛውንም ዓይነት የጦር መሣሪያ ዝውውር አንታገስም” ሲል ዝግጁነቱን ገልጿል።

በሌላ በኩል የሁቲ ወገኖች በጥቃቱ ሳቢያ በወደቡ የንግድና የእርዳታ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል መፈጠሩን በመጥቀስ ድርጊቱን አውግዘዋል።

የዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች በበኩላቸው ይህ አዲስ ግጭት ቀድሞውኑ በከፋ የሰብአዊ ቀውስ ውስጥ ለምትገኘው የየመን ሕዝብ የምግብና የመድኃኒት አቅርቦት ላይ ተጨማሪ ጫና እንዳይፈጥር ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

የወደቡ መጎዳት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የየመን ዜጎችን የዕለት ተዕለት ሕይወት አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችልም ድርጅቶቹ አስጠንቅቀዋል።

እስካሁን ባለው መረጃ በጥቃቱ የደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋትም ሆነ የንብረት ውድመት ዝርዝር መረጃ በግልጽ አልታወቀም። ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተልን ለእናንተ የምናደርስ ይሆናል።

ሱፊያን አህመድ

ታህሳስ 21/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *