“አርሶ አደሩ መሬቱን ለፋይናንስ ዋስትና በመጠቀም የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱን ሊያረጋግጥ እንደሚገባ ተገለጸ”

በኢትዮጵያ የሚተገበሩ የመሬት ፖሊሲዎች አርሶ አደሩ መሬቱን እንደ ዋና የኢኮኖሚ ካፒታል በመጠቀም የፋይናንስ አቅሙን የሚያሳድግበትን መንገድ ማመቻቸት እንዳለባቸው የመሬት አስተዳደር ተመራማሪ ዶ/ር ባጫ ደበሌ ይናገራሉ።

ዶ/ር ባጫ በጉዳዩ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፣ መሬት ለአርሶ አደሩ ከእለት ጉርስ ማግኛነት ባለፈ ለትላልቅ ኢንቨስትመንቶች እንደ ዋስትና (Collateral) ሊያገለግል የሚችል ትልቅ ሀብት መሆኑን ጠቁመዋል።

አርሶ አደሩ መሬቱን ሳይለቅ በባለቤትነት ይዞ፣ ከፋይናንስ ተቋማትና ከባንኮች ብድር የሚያገኝበት ህጋዊ ማዕቀፍ ሊዘረጋ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ተመራማሪው አክለውም፣ የከተማ መስፋፋትና የልማት ስራዎች በሚከናወኑበት ወቅት አርሶ አደሩን በልማት ሂደቱ ውስጥ ቀጥተኛ ባለድርሻ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ይህም አርሶ አደሩ መሬቱን ለባለሀብቶች በሽርክና በመስጠት ወይም በረጅም ጊዜ ኪራይ በማከራየት ዘላቂ ገቢ የሚያገኝበትን እድል እንደሚፈጥር አስረድተዋል።

በተጨማሪም፣ ዶ/ር ባጫ በትንታኔያቸው የመሬት አስተዳደር ፖሊሲዎች እንደየአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ ሊቃኙ እንደሚገባ ጠይቀዋል።

ፖሊሲዎች የአርሶ አደሩን የመሬት መብት ወደ ፋይናንስ አቅም በመለወጥ፣ የገጠሩን ማህበረሰብ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ማድረግ እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

በመጨረሻም፣ መሬትን እንደ ፋይናንስ መሳሪያ የመጠቀም ስልት ለአርሶ አደሩም ሆነ ለሀገር ኢኮኖሚ አዲስ የብልጽግና በር የሚከፍት መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ባጫ ደበሌ፣ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ለአለም አሰፋ

ታህሳስ 21/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *