የዩናይትድ ኪንግደም (UK) የመከላከያ ኤታማዦር ሹም ሪቻርድ ናይተን፣ ሀገሪቱ በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ውስጥ እስከ 37.6 ቢሊዮን ዶላር (28 ቢሊዮን ፓውንድ) የሚደርስ ከፍተኛ የመከላከያ በጀት ጉድለት ሊያጋጥማት እንደሚችል ለጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
ዘ ታይምስ የተሰኘው ጋዜጣ የውስጥ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ይህ ግዙፍ የፋይናንስ ክፍተት የተከሰተው የመከላከያ ኢንቨስትመንት ዕቅዶች ከሚጠበቀው በጀት በላይ በመሆናቸው ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር በጉዳዩ ላይ ከፍተኛ ቅሬታቸውን መግለጻቸው ተነግሯል።
ስታርመር ቀደም ሲል የቀረበው ስትራቴጂያዊ የመከላከያ ክለሳ ሁሉንም ወጪዎች ያካተተ እንደሆነ ቢያምኑም፣ አሁን የተገኘው መረጃ ግን የፋይናንስ ስሌቱ መዛባቱን አመላክቷል።
በዚህም ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመከላከያ ኢንቨስትመንት ዕቅዱ በድጋሚ እንዲታይ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
ይህ መመሪያ የመከላከያ ዘመናዊነት ስራዎች የሚተገበሩበትን ሂደት በዝርዝር የሚያስቀምጥ ሲሆን፣ ቀደም ሲል በፈረንጆቹ ታህሳስ ወር (ከገና በፊት) ለህዝብ ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቅ ነበር።
ሆኖም አሁን ባለው የበጀት ቀውስ ምክንያት ህትመቱ እስከ መጋቢት ወር (March) ሊዘገይ እንደሚችል ተመልክቷል።
የዩኬ መንግስት የመከላከያ ወጪውን እ.ኤ.አ. እስከ 2027 ድረስ ከሀገሪቱ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) 2.5 በመቶ ለማድረስ ማቀዱ ይታወሳል።
የዚህ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ዋነኛ አካል የሆነው የኒውክሌር ጦር መሳሪያን የማዘመን መርሃ ግብር ሲሆን፣ ለዚህም ብቻ 20 ቢሊዮን ዶላር ለመመደብ ታቅዶ ነበር።
ይህ አዲስ የበጀት ጉድለት ስጋት፣ የስታርመር መንግስት በብሄራዊ ደህንነት እና በኢኮኖሚ መረጋጋት መካከል ያለውን ሚዛን ለመጠበቅ በሚያደርገው ጥረት ላይ ትልቅ ፈተና ደቅኗል።
ልኡል ወልዴ
ጥር 01/2018 ዓ.ም
