በጠለምት ወረዳ የተጠለሉ ተፈናቃዮች ምንም አይነት ዕርዳታ እየተደረገላቸዉ አለመሆኑ ተገለጸ

በጠለምት ወረዳ ከትግራይ እና ከሌሎች ክልሎች ተፈናቅለው የሚገኙ ዜጎች ላለፉት ወራት ምንም አይነት ሰብዓዊ እርዳታ እያገኙ እንዳልሆነ የወረዳው አደጋ መከላከልና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን መሪ አቶ መሠረት ጥላሁን ገልጸዋል፡፡

አቶ መሠረት እንደገለፁት፤ በወረዳው ውስጥ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የተጠለሉ ተፈናቃዮች ያሉ ሲሆን፤ እነዚህ ወገኖች ካለፈው መስከረም ወር ወዲህ በተቋማትም ሆነ በመንግስት በኩል ምንም አይነት ድጋፍ እየተደረገላቸዉ እንዳልሆነ ተገልጿል።

በወረዳው ከ4መቶ21 በላይ አባወራዎች ወይም በድምሩ 2 ሺህ የሚጠጉ የቤተሰብ አባላት ያሏቸው ተፈናቃዮች በህብረተሰቡ ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ ተብሏል፡፡

እነዚህ ተፈናቃዮች ቀደም ሲል በአንዳንድ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች የምግብ እና የገንዘብ ድጋፍ ሲደረግላቸው የቆየ ቢሆንም፤አሁን ላይ ግን ምንም አይነት እርዳታ አለመኖሩን ሀላፊዉ ገልጸዋል።

ለእርዳታው መቋረጥ እንደ ምክንያት የተነሳው፤ ተፈናቃዮቹ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ በመንግስት በኩል አቅጣጫ መቀመጡና ተፈናቃዮቹ በበኩላቸው “የፀጥታ ችግር ስላለብን ወደመጣንበት አንመለስም” ብለው በቦታው በመቆየታቸው መሆኑን ኃላፊው አብራርተዋል፡፡

በወረዳው በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከ62 ሺህ በላይ ነዋሪዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚሹ በመሆናቸው፤ማህበረሰቡ ቀደም ሲል ለተፈናቃዮቹ ያደርግ የነበረውን መረዳዳት እና ማጋራት መቀጠል የማይቻልበት ደረጃ ላይ መድረሱ ተነግሯል፡፡

በመሆኑም የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት እና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ለተፈናቃዮቹም ሆነ በድርቅ ለተጎዳው የወረዳው ነዋሪ ትኩረት እንዲሰጡ ጥሪ ቀርቧል፡፡

ሊዲያ ደሳለኝ

ጥር 08/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *