በኢትዮጵያ የክትባት አይነቶችና ሽፋን መሻሻል ቢያሳዩም፤ በተደራሽነትና በባለሙያዎች ተነሳሽነት ረገድ አሁንም ሰፊ ክፍተቶች መኖራቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታዉቋል።
ኢትዮጵያ የምትሰጣቸውን የክትባት አይነቶች ከ6 ወደ 15 በማሳደግና ምንም ክትባት ያላገኙ ህጻናትን ቁጥር በመቀነስ ረገድ ውጤት ብታስመዘግብም በሀገሪቱ ካሉ 1ሺህ2መቶ9 ወረዳዎች መካከል እስካሁን የቅድመ ወባ ክትባት አገልግሎት ማግኘት የቻሉት ግን 58ቱ ብቻ ናቸው ተብሏል፡፡
እንዲሁም ስልጠና የወሰዱ ባለሙያዎች ጭምር በተለያዩ ምክንያቶች ክትባት ለመስጠት ወደኋላ የማለት ዝንባሌ ማሳየታቸው ለተደራሽነቱ እንቅፋት መሆኑ ተገልጿል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ዶ/ር ሴና ዱጋሳ ፤ክትባት እስከ አንድ ዓመት ላሉ ህጻናት ብቻ እንደሆነ ተደርጎ የሚታሰበው የተሳሳተ ግንዛቤ ሊቀየር ይገባልም ብለዋል፡፡
የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻልም በከተሞች በሚገኙ ኮንዶሚኒየሞች “ጊዜያዊ የክትባት ጣቢያዎችን” መክፈት እና የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎችለሚገኙ ዜጎች “ሂት ኤንድ ራን” (Hit and Run) የተሰኘውን ፈጣን የክትባት አሰጣጥ ስልት ለመጠቀም መታቀዱ ተጠቅሷል፡፡
በተጨማሪም ትክክለኛ የሕፃናት ቆጠራ በማካሄድና የባለሙያዎችን አመለካከት በመገንባት ፕሮግራሙን ውጤታማ ለማድረግ አቅጣጫ መቀመጡን ጣቢያችን ሰምቷል፡፡
ሀና ሰይፉ
ጥር 08/2018 ዓ.ም
