ለጤና አደገኛ የሆነ እና ባእድ ነገር ተቀላቅሎ ሊፈጭ የነበረን 23 ኩንታል እርድ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተነግሯል፡፡
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን በጅማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት፤ጅማ ከተማ ለምግብነት የማይውል “የምግብ እርድ” ከበቆሎ ጋር ቀላቅሎ ሲያስፈጭ የነበረ ወፍጮ ቤት ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል።
ይህ 23 ኩንታል ከበቆሎ ጋር የተቀላቀለ እርድ ግምታዊ ዋጋ ከ3መቶ45 ሺህ ብር በላይ ነው ተብሏል።
ህገወጥ ተግባሩ ሊያዝ የቻለው ጥር 5 ቀን 2018 ዓ.ም ከጥምቀት በዓል በፊት በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ መሆኑን ጣቢያችን ሰምቷል።
ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ በከተማዋ በሚገኙ ወፍጮ ቤቶች፣ የቅቤ እና የማር መሸጫዎች ላይ ባደረገው የጥራት ቅኝት፣ ይህ ለጤና አደገኛ የሆነ ምርት ለገበያ ሳይሰራጭ ቀድሞ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተጠቅሷል።
ድርጊቱን ሲፈጽም የተገኘው ወፍጮ ቤትም የታሸገ ሲሆን፤ተገቢው የሕግ እርምጃ እየተወሰደበት ይገኛል ተብሏል።
ባለስልጣኑ በተለይ በበዓላት ወቅት መሰል ህገወጥ ተግባራት እና የምግብ ማጭበርበሮች ስለሚበራከቱ፣ ቁጥጥሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለፀ ሲሆን፤ ህብረተሰቡም የሚገዛቸውን የምግብ ምርቶች ጥራትና ደህንነት በጥንቃቄ እንዲመረምር እና አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከት ለሚመለከተው አካል እንዲጠቁም አሳስቧል።
ሐመረ ፍሬው
ጥር 08/2018 ዓ.ም
