በብራዚል ኩሪቲባ ከተማ የሚኖር አንድ ግለሰብ የጓደኞቹንና የዘመዶቹን ታማኝነት ለመፈተን ሲል የራሱን የሐሰት ሞት አውጆ የቀብር ሥነ-ሥርዓቱን ለማከናወን ተሰናዳ።
እ.ኤ.አ 2023 ባልታዛር ሌሞስ የተባለ የ60 ዓመት ግለሰብ፣ በማህበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ በሳኦ ፓውሎ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ለሕክምና መግባቱን የሚገልጽ ፎቶግራፍ ለጥፎ ለወዳጅ ዘመዶቹ አሳወቀ ታዲያ ምንም ያህል ሳይቆይ ማግስቱን “ባልታዛር ሌሞስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፣ ” በማለት እና የሚቀበርበትን ቤተክርስቲያን በመጥቀስ የመሞቱን ዜና በገጹ ላይ ለጠፈ።
ዜናውን የሰሙ ቤተሰቦች፣ የቅርብ ጓደኞችና የሥራ ባልደረቦች በከፍተኛ ድንጋጤና ሐዘን ወደ ተጠቀሰው ቤተክርስቲያን አመሩ ታዲያ በቦታው ሲደርሱ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ የሟች ፎቶ ተቀምጦና የሐዘን ሙዚቃ ተከፍቶ ነበር የጠበቃችው ወዳጆቹ በከፍተኛ ድንጋጤ እና ሀዘን ውስጥ በነበሩበት ወቅት በድንገት የባልታዛር ድምፅ በድምፅ ማጉያ ተሰማ።
በመጀመሪያ ታዳሚው ሟች አስቀድሞ የቀረጸው የስንብት መልዕክት መስሏቸው የነበረ ቢሆንም፣ ባልታዛር በድንገት ከቤተክርስቲያኑ የኋላ በር ብቅ በማለት ወደ መድረኩ ሲያመራ ሁሉም በድንጋጤ ደርቀው ቀርተዋል።
ግለሰቡ ፈገግ ብሎ “እኔ በሕይወት አለሁ” ማለቱን ተከትሎ፣ በለቅሶ ላይ የነበሩ ሰዎች በከፍተኛ ቁጣና ግራ መጋባት ውስጥ እንዲገቡ ሆነዋል።
ባልታዛር ለድርጊቱ በሰጠው ምላሽ “ባለፉት ሁለት ዓመታት በመቶዎች የሚቆጠሩ የቀብር ሥነ-ሥርዓቶችን መርቻለሁ። አንዳንዶቹ ላይ 2 ሰው ብቻ ሲመጣ፣ ሌሎቹ ላይ ደግሞ 500 ሰው ይታደማል። እኔ ስሞት እነማን እንደሚመጡና በእርግጥም የሚወዱኝ ሰዎች እነማን እንደሆኑ በዓይኔ ማየት ፈልጌ ነው” ብሏል።
ድርጊቱን በብራዚል መገናኛ ብዙኃንና ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ የዘገቡት ሲሆን ስለጉዳዩ የሰሙ ሰዎች ድርጊቱን “ጭካኔ የተሞላበት ቀልድ” ሲሉ ተችተውታል። የባልታዛር የእህት ልጅ ለጋዜጠኞች በሰጠችው ቃል “ሁላችንም በጣም ደንግጠን ነበር፣ ይህ ፈጽሞ ሊደረግ የማይገባ ቀልድ ነው” ስትል ቅሬታዋን ገልጻለች።
ሊዲያ ደሳለኝ
ጥር 14/2018 ዓ.ም
