የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ በዩክሬን ሰላም ዙሪያ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ጋር ሊወያዩ ነው

የአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍና የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አማች ጃሬድ ኩሽነር በዩክሬን የሰላም ሁኔታ ላይ ለመወያየት ዛሬ በሞስኮ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር እንደሚገናኙ ተናግረዋል።

በስዊዘርላንድ ዳቮስ ከተማ እየተካሄደ ካለው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ጎን ለጎን ከዩክሬን ባለሥልጣናት ጋርም ውይይት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

በጉዳዩ ላይ የሚደረጉት ሁሉም ስብሰባዎች በጥሩ ሁኔታ እንደሚሄዱ ተስፋ አደርጋለሁ። ሰላም ያስፈልገናል ብለዋል ልዩ መልዕክተኛዉ።

ዊትኮፍ ለ4 ዓመታት ገደማ የዘለቀውን የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ለማቆም የሚያስችለውን ስምምነት የመጨረሻ 10 በመቶ ላይ ለመድረስ መቃረባቸውን ገልጸዋል።

ኪቭ በአብዛኛው የሰላም እቅድ ላይ መስማማቷን ብትገልጽም፤ አስቸጋሪው የግዛት ጥያቄን ጨምሮ ቁልፍ ጉዳዮች አሁንም እንዳልተፈቱ ተናግራለች።

በተጨማሪም ዩክሬን፤ ሞስኮ በድጋሚ ጥቃት እንዳትሰነዝር ለመከላከል ወሳኝ ናቸው ስለምትላቸው ከጦርነት በኋላ የሚሰጡ የደህንነት ዋስትናዎች ላይ ከአጋሮቿ ግልጽ ማብራሪያ እየፈለገች ነው።

ይህ የሰላም ንግግር እየተካሄደ ያለው ሞስኮ በብርቱው የክረምት ወቅት የዩክሬንን የኃይል መሠረተ ልማቶች መምታቷን በቀጠለችበት ወቅት ነው።

ዋሽንግተን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በአውሮፓ ውስጥ የተከሰተውን እጅግ አስከፊ ግጭት ለማቆም ስምምነት ላይ ለመድረስ የምታደርገውን ጥረት ከቅርብ ወራት ወዲህ አጠናክራለች ያለዉ ኤኤፍ ፒ የዜና ወኪል ነዉ።

እስከዳር ግርማ

ጥር 14/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *