በስድስት ሜትር ርዝመት ባለው የብረት የኤሌክትሪክ ምሰሶ ውስጥ አልፎ በማደግ፣ በሌላኛው ጫፍ ለምለም ቅጠሎችን ያወጣው የቀርከሃ ተክል በቻይና የጥንካሬ እና የጽናት ምልክት ሆኗል።
በቻይና ዢጂያንግ ግዛት ዢንቻንግ ካውንቲ በሚገኘው የዓለም የንግድ ማዕከል አቅራቢያ፣ አንድ ቀጭን የቀርከሃ ተክል በብረት ምሰሶ ውስጥ አልፎ ሲያድግ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል (ቪዲዮ) በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ተሰራጭቷል።
“የማይበገረው ቀርከሃ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ብርቱ ተክል፣ ከምሰሶው ጥቂት ሴንቲ ሜትር ርቀት ላይ በመብቀል በምሰሶው ግርጌ በሚገኝ ትንሽ ቀዳዳ በኩል ወደ ውስጥ ዘልቆ መግባት ችሏል።
አብዛኞቹ ተክሎች ሙሉ በሙሉ ጨለማ በሆነ ቦታ ውስጥ በደንብ ማደግ ባይችሉም፣ ይህ ቀርከሃ ግን ሁኔታውን በሚገባ የተቋቋመው ይመስላል፤ ምክንያቱም የምሰሶውን ጫፍ እስከሚነካ ድረስ አድጎ ለምለም አረንጓዴ ቅጠሎችን አውጥቷል።
ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፣ ቀርከሃ በጨለማ ውስጥ ሊያድግ የሚችለው ሰፊና በደንብ የዳበረ የሥር ሥርዓት ስላለውና ከመሬት በታች ያሉ ግንዶቹ ውሃና ንጥረ ነገሮችን ከአፈር ውስጥ በጥልቀት በመምጠጥ ብርሃን በሌለበት የመጀመሪያ ደረጃ ላይ እድገቱን እንዲቀጥል ስለሚያስችሉት ነው።
ሰዎች ተአምሩን በአካል ለማየት ወደ ቦታው መሄድ የጀመሩ ሲሆን፣ አንዳንዶች ደግሞ ለልጆቻቸው ስለ ጥንካሬ፣ ስለ ጽናት እና ስለ ሕይወት ብርታት ትምህርት ለመስጠት ወደዚያ ይዘዋቸው ይሄዳሉ ሲል ኢዲቲ ሴንትራል ዘግቧል፡፡
ሐመረ ፍሬው
ጥር 15/2018 ዓ.ም
