በሪል እስቴት ዘርፍ የቤት ገዥዎችን ዋስትና የሚያረጋግጥ አዲስ ስምምነት ተፈረመ

በኢትዮጵያ የሪል እስቴት ዘርፍ ለዓመታት የዘለቀውን የቤት ገዥዎች እሮሮ ለመፍታትና በአልሚዎች ላይ የሚነሳውን የቅሬታ ማዕበል ለመግታት የሚያስችል አዲስ ስምምነት ተፈርሟል።

የኢትዮጵያ ሪል እስቴት አልሚዎች ማህበር እና የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት፣ በዘርፉ ግልፅነትና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችል የቃል ኪዳን ሰነድ ተፈራርመዋል።

የቤት ፍላጎት በናረበት በዚህ ወቅት፣ በርካታ ዜጎች በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘባቸውን ከፍለው ዓመታትን ቢጠብቁም ቤታቸውን መረከብ አለመቻላቸውና የኑሯቸው መናጋት የዘርፉ ዋነኛ ችግር ሆኖ ቆይቷል።

የተፈረመው የሁለትዮሽ ስምምነትም ይህንን ስር የሰደደ “የታማኝነት ጉድለት” ለመቅረፍና የገዥዎችን መብት በህግ ለመጠበቅ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

ይህ አዲስ ስምምነት ከቀደሙት አሰራሮች የሚለይባቸው ሶስት ዋና ዋና ነጥቦች የተለዩ ሲሆን፤
ስምምነቱ በቅርቡ የፀደቀውን የሪል እስቴት ልማትና አስተዳደር አዋጅ በቀጥታ ወደ ተግባር የሚቀይር በመሆኑ የመንግስት ሙሉ እውቅና አለው።

ሌላኛው የቤት ፈላጊዎች ከገንዘብ ብክነትና ከተለያዩ የማጭበርበር ድርጊቶች ነፃ ሆነው በገቡት ውል መሰረት ቤታቸውን በተገቢው ጊዜ እንዲረከቡ የሚያረጋግጥ ጥብቅ ስትራቴጂ ይከተላል።

በሻጭና በገዥ መካከል አለመግባባት ሲፈጠር በረጅም የፍርድ ቤት ክርክር ከመንገላታት ይልቅ፣ በግልግል ዳኝነት አማካኝነት ፈጣንና ፍትሃዊ መፍትሄ እንዲያገኙ ያደርጋልም ተብሏል።

የኢትዮጵያ ሪል እስቴት አልሚዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አለማየሁ ከተማ፤በዘርፉ በአሉታዊ መልኩ ስምን የሚያጎድፉ ድርጊቶች በአልሚዎችም ሆነ በሌሎች አካላት ሲፈጸሙ መቆየታቸውን አምነዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም “ገንዘባቸውን ከፍለው ቤት ባለማግኘታቸው ኑሯቸው የተናጋባቸው ዜጎች መኖራቸው የማህበሩ ትልቅ ስጋት ነው” ብለዋል።

በመሆኑም ማንኛውም በዘርፉ የሚሳተፍ አልሚ የስነ-ምግባር ደንቡን እንዲፈርምና እንዲያከብር እንደሚደረግ፣ ከስርአት ውጭ የሚሰሩትም ወደ መስመር እንዲገቡ ጥብቅ ክትትል እንደሚደረግ አንስተዋል።

ከትናንት ጥር 14/2018 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሆነው ይህ የቃል ኪዳን ሰነድ፣ የጠፋውን የገዥዎች እምነት በመመለስ ረገድ በኢትዮጵያ የሪል እስቴት ገበያ ላይ አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

ልዑል ወልዴ

ጥር 15/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *