የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የስድስት ወራት የስራ ግምገማውን ባደረገበት ወቅት ባቀረበው ሪፖርት 16.453 ጊጋ ዋት የኤሌክትሪክ የኃይል ሽያጭ 246 ሚሊየን ዶላር መገኘቱን አስታውቋል።
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስትራቴጂክ ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚ አቶ አለሙ መንገሻ ባቀረቡት ሪፖርት እንዳሉት በስድስት ወራት ውስጥ ለማግኘት ታቅዶ ከነበረው 202.20 ሚሊዮን ዶላር ከፍ ያለ የሽያጭ ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል ።
ኢትዮጵያ ፍላጎት ላሳዩና ለሌሎች ሃገራት በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርት በማድረግ ለአገሪቱ የውጪ ምንዛሬ ከሚያስገኙ ዘርፎች አንዱ ለማድረግ በርካታ ስራዎችን እያከናወነች እንደምትገኝ አቶ አለሙ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናን በኃይል ትስስር ለማጠናከር በያዘችው ዕቅድ መሰረት ከኬንያ ፣ከጅቡቲ ፣ሱዳን እና ታንዛኒያ የኤሌክትሪክ የኃይል ትስስር ፈጥራለች።
ከውሃ ሃይል፣ ነፋስ፣ እንፋሎት፣ የጸሃይ ብርሃንንን በመጠቀም የንጹህ ኃይል አምራች ለመሆን እቅድ ይዛ ያለችው ኢትዮጵያ በዚህም ማሳካት የምትፈልገው ከምስራቅ አፍሪካ ባሻገር የአፍሪካ የኃይል ምንጭ ማዕከል መሆንን ነው።
ያይኔ አበባ ሻምበል
ጥር 15/2018 ዓ.ም
