አሜሪካ ከዓመት በፊት በሰጠችው ቅድመ ማስጠንቀቂያ መሠረት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል ከሆነው የዓለም የጤና ድርጅት አባልነት በይፋ ለቅቃ ወጣች።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሁለተኛ ዙር የሥልጣን ዘመናቸውን በጀመሩበት ዕለት ካስተላላፏቸው ፕሬዝዳንታዊ ውሳኔዎች መካከል አንዱ የሆነው ከዓለም ጤና ድርጅት መውጣት ተግባራዊ ሆኗል።
ይህንን ውሳኔ ተከትሎ የአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማ ስዊዘርላንድ ጄኔቫ ከሚገኘው የዓለም የጤና ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት እንዲነሳ መደረጉን ሮይተርስ የዜና ወኪል የዓይን እማኞችን ጠቅሶ ዘግቧል።
ከአሜሪካ ጤና እና የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቶች በጋራ በወጣው መግለጫ መሠረት፤ ከዚህ በኋላ አገሪቱ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር የሚኖራት ግንኙነት ውስን እና ከተቋሙ መውጣቷን ለማጠናቀቅ በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ እንደሚሆን ተጠቅሷል።
አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ መንግሥት የጤና ባለሥልጣን “በድርጅቱ ውስጥ በታዛቢነት የመሳተፍም ሆነ መልሶ አባል የመሆን ዕቅድ የለንም” ሲሉ ተናግረዋል።
በበሽታዎች ቁጥጥር እና ቅድሚያ በሚሰጣቸው በሌሎች የኅብረተሰብ ጤና ጉዳዮች ላይ በዓለም አቀፍ ድርጅት በኩል ሳይሆን በቀጥታ ከአገራት ጋር ለመሥራት አቅዳለች።
በኢትዮጵያዊው ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም የሚመራው እና ከ1መቶ90 በላይ አገራትን በአባልነት ከያዘው ተቋም አሜሪካ ለመውጣት መወሰኗ በአሜሪካ እንዲሁም በቀሪው የዓለም ክፍል የሚከናወኑ የጤና ሥራዎችን የሚጎዳ መሆኑ እየተነገረ ነው።
አሜሪካ እራሷን ያገለለችው ከዓለም ጤና ድርጅት ብቻ ሳይሆን በቅርቡ ከበርካታ የመንግሥታቱ ድርጅት አካላት ከሆኑ ተቋማት ለመውጣት ከመወሰኗ በተጨማሪ፣ የሰላም ቦርድ በማለት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ያስተዋወቁት ስብስብ የተባበሩት መንግሥታትን ሚና የሚያዳክም ነው በሚል እየተተቸ ይገኛል ያለዉ ቢቢሲ ነዉ።
ጥር 15/2018 ዓ.ም
