ቲክቶክ አዲስ የአሜሪካ ተቋም ለመመስረት የሚያስችለውን ስምምነት አጠናቀቀ

ቲክቶክ በአሁኑ ወቅት ከ2መቶ ሚሊየን በላይ አሜሪካውያን ይጠቀሙበታል

ለዓመታት ሲያሰጋው የነበረውንና በአሜሪካ ሊጣልበት የነበረውን የእገዳ ስጋት በማስወገድ አዲስ የአሜሪካ ተቋም ለመመስረት የሚያስችለውን ስምምነት አጠናቋል።

ኩባንያው ባወጣው መግለጫ፤ አዲሱ የቲክቶክ ስሪት “ሁለንተናዊ የመረጃ ጥበቃን፣ የአልጎሪዝም ደኅንነትን፣ የይዘት ቁጥጥርን እና ለአሜሪካ ተጠቃሚዎች የሶፍትዌር ዋስትናን በመስጠት ብሔራዊ ደኅንነትን በሚያስጠብቁ ግልጽ ጥበቃዎች” ሥር ይሠራል ብሏል።

አሜሪካውያን የቲክቶክ ተጠቃሚዎችም ያንኑ መተግበሪያ መጠቀም መቀጠል ይችላሉ።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ስምምነቱን ያደነቁ ሲሆን፤ የቻይናውን መሪ ሺ ጂንፒንግን “ከእኛ ጋር ስለሠሩና በመጨረሻም ስምምነቱን ስላጸደቁ” በተለየ ሁኔታ አመስግናለሁ ብለዋል።

ትራምፕ አክለውም “ወደፊት ቲክቶክን በሚጠቀሙና በሚወዱ ሰዎች ዘንድ ለረጅም ጊዜ እንደምታወስ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ ጽፈዋል፡፡

ይህ ስምምነት በአሜሪካ ውስጥ ከፍተኛ ተወዳጅነት ያለው የቲክቶክ መተግበሪያ ዕጣ ፈንታ ላይ ለዓመታት የቆየውን አለመረጋጋት እንዲያበቃ ያደርጋል፡፡

በኮንግረስ ውስጥ የሁለቱም ፓርቲዎች አባላት በከፍተኛ ድምፅ ያጸደቁትና ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የፈረሙት ሕግ፤ ቲክቶክ ከቻይናው ባይትዳንስ ተለይቶ አዲስ ባለቤት ካላገኘ በስተቀር እንዲታገድ የሚደነግግ ነበር።

በዚህም መሠረት እስከ ጥር 2025 የጊዜ ገደብ ድረስ እንዲዘጋ ተወስኖ ነበር።

ለጥቂት ሰዓታትም ተዘግቶ የነበረ ቢሆንም ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሥልጣን የመጀመሪያ ቀናቸው፣ አስተዳደራቸው የኩባንያውን የሽያጭ ስምምነት እስኪያጠናቅቅ ድረስ ቲክቶክ ሥራውን እንዲቀጥል የሚያስችል አስፈጻሚ ትዕዛዝ ፈርመዉ እንደነበር ኤቢሲ ኒዉስ አስታዉሷል።

እስከዳር ግርማ

ጥር 15/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *