ባለፉት ጊዜያት በተለያዩ ዙሮች በአማራ ክልል ብቻ ከ13 ሺህ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ሰላም ተመልሰው በ DDR ፕሮግራም እንዲያልፉ ተደርጓል ተብሏል።
እስከአሁን ድረስ አስተዳደራዊ ወጪዎችን ሳይጨምር በአማራ ክልል ለቀድሞ ተዋጊዎች የመልሶ ማቀላቀል ክፍያ ብቻ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ወጭ መደረጉን የብሄራዊ ተሃድሶ ኮምሽን ተናግሯል።
ከ83 ሺህ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎችን በተሃድሶ እንዲያልፉ በማድረግና መልሶ ማቀላቀል መቻሉን ኮምሽኑ ገልፆል።
ከዚህ ዉስጥ በትግራይ ÷ በአማራ እና ኦሮሚያ እንዲሁም በአፋር ክልሎች የተደረገ ነዉ ተብሏል።
ኮሚሽኑ እንደሚገልፀዉ ከሆነ በተደረገ የመጀመሪያ ደረጃ ጥናት በሀገሪቱ ሰባት ክልሎች ከ 3 መቶ 71 ሺህ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎች ተለይተዋል ሲል ገልፆል።
በዚህ ስራ ዉስጥ ከመንግሥት እና ከልማት አጋሮች ተገኝቷል በተባለ ሀብት ከ10 ቢሊዩን ብር በላይ ዉጪ መደረጉን የብሔራዊ ተሃድሶ ኮምሽን አስታዉቋል።
በአማራ ክልል በየትኛውም አካባቢ ያሉ ታጣቂዎች የህዝብና የመንግስትን የሰላም ጥሪን ተቀብለው ትጥቅ እንዲያስረክቡ እና የተሃድሶ ፕሮግራሙ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል ፡፡
የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት (አፋህድ) ከፍተኛ አመራሮች ከክልሉ መንግስት ጋር ያደረጉትን የሰላም ስምምነት መሰረት በማድረግ ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ከፍተኛ የአፋህድ አመራሮችና አባሎቻቸው ይፋዊ የጦር መሳሪያ ርክክብ እንዲያደርጉ ማድረጉን ተናግሯል።
በተጨማሪም የተሃድሶ ስልጠና እንዲወስዱ እና በመልሶ ማቀላቀል ሂደት እንዲያልፉ እያደረገ ስለመሆኑ አያይዞ ገልፆል፡፡
ቁምነገር አየለ
ጥር 19/2018 ዓ.ም
