እስራኤል በግብፅ እና በጋዛ መካከል ያለውን የራፋህ መሻገሪያ በተወሰነ መልኩ ለመክፈት ተስማማች

እስራኤል የዶናልድ ትራምፕ የሰላም ዕቅድ አካል በሆነው ስምምነት መሠረት፤ በጋዛ ሰርጥ እና በግብፅ መካከል ያለውን የራፋህ የድንበር መሻገሪያ በተወሰነ መልኩ ዳግም ለመክፈት መስማማቷን አስታውቃለች።

እሁድ ምሽት ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የወጣው መግለጫ እንደሚያመለክተው፤ መሻገሪያው ክፍት የሚሆነው ለእግረኞች ማለፊያ ብቻ ሲሆን፤ ይህም በእስራኤል ሙሉ የፍተሻ ሥርዓት ስር የሚከናወን ይሆናል።

የራፋህ መሻገሪያ ወደ ጋዛ ለሚገባ የሰብአዊ እርዳታ ዋነኛ መግቢያ ነው። መሻገሪያው ከግንቦት 2024 ጀምሮ በአብዛኛው ተዘግቶ ቆይቷል።

የሰብአዊ ድርጅቶች እና የተባበሩት መንግሥታት መሻገሪያው እንዲከፈት ለረጅም ጊዜ ሲጠይቁ የቆዩ ቢሆንም፤ የእስራኤል ባለሥልጣናት ግን ከጥቅምት 10 ጀምሮ የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ ከሆነ በኋላም እንኳ መሻገሪያው እንዳይከፈት ሲከለክሉ ቆይተዋል።

ባለሥልጣናቱ የመሻገሪያው ዳግም መከፈት በሕይወት ያሉ እና የሞቱ ታጋቾች በሙሉ ከመመለሳቸው ጋር የተያያዘ ‹‹ቅድመ ሁኔታ›› መሆኑን ገልጸው ነበር።

ሰኞ ዕለት እስራኤል ራን ግቪሊ የተባለ የፖሊስ መኮንን የሆነውን የመጨረሻውን ታጋች አስከሬን ከጋዛ ማውጣቷን አስታውቃለች።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የራን ግቪሊ አስከሬን መገኘቱን ለእስራኤል እና ለወታደሮቿ አስደናቂ ስኬት ነዉ ሲሉ ገልጸውታል።

የተባበሩት መንግሥታት የመጨረሻው እስራኤላዊ ታጋች አስከሬን መገኘቱን በደስታ የተቀበለ ሲሆን፤የጋዛው የተኩስ አቁም ዕቅድ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን ጥሪ አቅርቧል።

እስከዳር ግርማ

ጥር 19/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *