በናይጄሪያ የቲኑቡን መንግሥት ለመገልበጥ አቅደዉ ነበር የተባሉ ወታደሮች ለፍርድ ሊቀርቡ ነው

የናይጄሪያ ጦር ኃይል ባለፈው ዓመት ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡን ከሥልጣን ለማውረድ አቅደዉ ነበር የተባሉ በርካታ መኮንኖችን ለፍርድ እንደሚያቀርብ አስታውቋል።

ይህም ቀደም ሲል መንግሥት አስተባብሎት የነበረውን የሴራ ጥንሰሳ አምኖ መቀበሉን ያሳያል።

ባለፈው ጥቅምት ወር፣ ወታደራዊው ኃይል 16 መኮንኖች በዲሲፕሊን ግድፈት ምክንያት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጾ ነበር።

ይፋዊ ማስተባበያዎች ቢሰጡም፣ በናይጄሪያ መንግሥት እና በወታደራዊው ክፍል ውስጥ ያሉ ምንጮች ግን መኮንኖቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ምክንያት መሆኑን ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረው ነበር።

የመከላከያ ዋና መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ሜጀር ጄኔራል ሰማኢላ ኡባ በሰጡት መግለጫ፤ የናይጄሪያ የታጠቀ ኃይል በጉዳዩ ላይ የተደረገው ምርመራ መጠናቀቁን ለሕዝብ ማሳወቅ ይፈልጋል ፤
ምርመራው መንግሥትን ለመገልበጥ በማሴር የተጠረጠሩ በርካታ መኮንኖችን ለይቷል ሲሉም አክለዋል።

ለችሎቱ የተቀጠረ ቀን ባይኖርም የሕግ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ መኮንኖቹ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ የሞት ቅጣት ሊጠብቃቸው ይችላል።

ቲኑቡ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውን ካስተባበሉ ከጥቂት ጊዜ በኋላ፤ በአገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ላይ የሹም ሽር አድርገው እንደነበር አፍሪካ ኒዉስ አስታዉሷል፡፡

እስከዳር ግርማ

ጥር 19/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *