ከሁለት አስርት ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ አልፎ አልፎ ሲካሄድ የቆየው ድርድር ተጠናቆ፣ የአውሮፓ ህብረት እና ህንድ ታሪካዊ የንግድ ስምምነት ማድረጋቸውን ሊያበስሩ ተቃርበዋል።
ሁለቱ ወገኖች ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ያለውን ውጥረት ተከትሎ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር አልመዋል ተብሉዋል።
የህንድ የንግድ ሚኒስቴር ፀሐፊ ራጄሽ አጋርዋል ሰኞ ዕለት እንደገለጹት፣ ድርድሩ ተጠናቆ ስምምነቱ የመጨረሻ ቅርፅ ይዟል።
በአሁኑ ወቅት የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን እና የአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አንቶኒዮ ሉዊስ ሳንቶስ ዳ ኮስታ ስምምነቱ ይፋ ይሆናል ተብሎ በሚጠበቅባት ዴልሂ ከተማ ይገኛሉ።
ህንድም ሆነች የአውሮፓ ህብረት ከዩናይትድ ስቴትስ የሚመጣባቸውን ኢኮኖሚያዊ እና ጂኦፖለቲካዊ ጫና ለመቋቋም ሲሉ ከቀሪው ዓለም ጋር ያላቸውን ስትራቴጂካዊ እና የንግድ ትስስር ለማጠናከር እየሰሩ ነው።
አሁን ላይ ህንድ ባለፈው ዓመት በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተጣለባትን የ50% ታሪፍ (ቀረጥ) ለመወጣት እየታገለች ሲሆን፣ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር የምታደርገው የንግድ ድርድር አሁንም እንደተጓተተ ነው።
ፕሬዝዳንት ኮስታ ሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ፣ አሜሪካን በስም ባይጠቅሱም “ይህ የንግድ ስምምነት ህንድ እና የአውሮፓ ህብረት ከታሪፍ ይልቅ በንግድ ስምምነቶች እንደሚያምኑ ለዓለም የሚያስተላልፉት ጠቃሚ የፖለቲካ መልዕክት ነው” ብለዋል።
ይህ ስምምነት የህንድ ምርቶች ወደ አውሮፓ በስፋት እንዲገቡ የሚያስችል ሲሆን፣ እንደ መኪና እና መጠጦች ያሉ የአውሮፓ ምርቶች እና ኢንቨስትመንቶች ደግሞ ወደ እስያ ሶስተኛ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ህንድ በቀላሉ እንዲገቡ መንገድ የሚከፍት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ እንደገለጹት፣ ይህ ስምምነት የዓለምን ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) 25% እና የዓለምን ንግድ አንድ ሶስተኛ ይወክላል።
የአውሮፓ ህብረት የህንድ ቀዳሚ የሸቀጦች ንግድ አጋር ሲሆን፣ በ2024-25 ብቻ የሁለትዮሽ የንግድ ልውውጡ 136 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።
ድርድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ በ2007 የተጀመረ ሲን ፣ በመኪና ገበያ፣ በግብርና ምርቶች እና ከካርቦን ልቀት ጋር በተያያዙ ታሪፎች ሳቢያ በ2013 ተቋርጦ ነበር ነገር ግን በተደረጉ ጥረቶች ድርድሩ በሐምሌ ወር 2022 በድጋሚ ተጀምሩዋል፡፡
አሁን ያሉ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት መደበኛው ፊርማ የሚከናወነው ስምምነቱ በአውሮፓ ፓርላማ እና በአውሮፓ ምክር ቤት ከጸደቀ በኋላ በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ይሆናል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው ።
ሀና ሰይፉ
ጥር 19/2018 ዓ.ም
