በዳቮስ ስዊዘርላንድ በተካሄደው የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ላይ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በአሜሪካ የገንዘብ ድጋፍ እየተገነባ መሆኑን በመጥቀስ የሰጡት አስተያየት፣ በኢትዮጵያ ምሁራን ዘንድ ጠንካራ ተቃውሞና ማረምያ እየቀረበበት ይገኛል።
ፕሬዝዳንቱ ግድቡ በአሜሪካ ገንዘብ መገንባቱንና የግድቡ መጠናቀቅ በተፋሰሱ የታችኛው አገራት ላይ ስጋት ሊፈጥር እንደሚችል መናገራቸው ቢሰማም፣ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና የዓባይ ወንዝ ተደራዳሪው ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ ግን ይህ የፕሬዝዳንቱ ንግግር መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር ፍፁም እንደማይገናኝ ገልጸዋል።
ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ እንደገለጹት፣ ግድቡ በአሜሪካ ገንዘብ እየተገነባ ነው የሚለው መረጃ መሰረተ ቢስ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ሙሉ ወጪና በዜጎች መዋጮ እየተገነባ ያለ ብሔራዊ ኩራት ነው።
ምሁሩ አክለውም ምናልባት ትራምፕም ሆኑ ሌላ አካል በእኛ ገንዘብ ተገነባ የሚሉ ከሆነ ስለ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሊሆን እንደማይችልና ሌላ እነሱ የሚያውቁት እኛ የማናውቀው ግድብ ካለ ወደፊት ልንሰማ እንችላለን በማለት የፕሬዝዳንቱን ንግግር በምላሽ አጣጥለውታል።
ግድቡ የታችኞቹን አገራት ውሃ ያስቀንሳል ተብሎ የሚነሳው ስጋትም ቢሆን የተሳሳተ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ያዕቆብ፣ ኢትዮጵያ በሉዓላዊ ግዛቷ ውስጥ የውሃ ልማቷን በከፍተኛ ጥንቃቄና ሌሎችን በማይጎዳ መልኩ እየሰራች መሆኑን አብራርተዋል።
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካውያን የራሳቸውን ሀብት በራሳቸው አቅም ማልማት እንደሚችሉ በተግባር ያስተማረ ትልቅ ፕሮጀክት መሆኑን ዶክተር ያዕቆብ አጽንኦት ሰጥተውበታል።
ለዓለም አሰፋ
ጥር 20/2018 ዓ.ም
