በጦርነት ዉስጥ በቆዩ አካባቢዎች ወጣቶች ያጋጠማቸው የአእምሮ ጤና ችግር የረባ አገልግሎት የሚያገኙበት አሰራር እንደሌለ ተገለፀ

መንግስታዊ ያልሆነ YOUNG LIVES ETHIOPIA የተባለ አለምአቀፍ ተቋም አዲስ አበባን ጨምሮ በ7 ክልሎች እና በሀያ የተለያዩ አካባቢዎች ደሃ ተኮር ጥናትን ሲያደርግ ቆይቷል።

ተቋሙ ከ25 አመት በፊት ጥናቱ ሲጀመር በፈረንጆች አቆጣጠር 2000 አመት ላይ የተወለዱ አሁን 25 አመት ላይ ያሉ እንዲሁም ጥናቱ ሲጀመር ሰባት አመት የነበሩ ህፃናት አሁን 31 አመት የሞላቸዉ ወጣቶች ላይ ንፅፅራዊ የሆነ አይነታዊ ጥናት እያካሄደ መቆየቱን ነግሮናል።

የ “YOUNG LIVES ” ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተሩ ዶ/ር አሉላ ፓንክረስት ከኢትዩ ኤፌም ጋር በነበራቸዉ ቆይታ እንደተናገሩት በዜሮ አመት እድሜ ጥናቱ 3 ሺህ ህፃናት ይዞ ቢጀምርም አሁን ላይ 2 ሺህ 500 በሆኑ ላይ እስከ 25 አመታቸዉ ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።

እነዚህ ህፃናት ወደ አዋቂነት የተሻገሩት በችግር ወቅት መሆኑን ጥናቱ አመላክቷል የሚሉት ዶ/ር አሉላ የኮቪድ 19 መምጣት ÷ ሀገሪቱ ወደ ጦርነት መግባት÷ የስራ አጥነት ከችግሮቹ ዉስጥ እንደሆኑ ገልፀዋል።

እነዚህ ችግሮች ወደ ወጣትነት ያደረጉትን ሽግግር ተግዳሮቶች የነበረዉ እንዲሆን ማድረጉን ዶ/ር አሉላ ፓንክረስት ይናገራሉ።

ጥናቱ በተለየ ሁኔታ በ7 ዙር በተመረጡ 7 አካባቢዎች ብቻ 500 ህፃናት ላይ ጠለቅ ያለ ጥናት አካሂዷል ተብሏል።

ዶ/ር አሉላ ከዛ ዉስጥ የአእምሮ ጤና ላይ ትኩረት ባደረገዉ ክትትል የአማራ እና ትግራይ ክልል እንደሚገኝ ይናገራሉ። የጦርነት እና ግጭት ተፅዕኖ ስለመታየቱ አንስተዋል።

በነዚህ አካባቢዎች ወጣቶች ያጋጠማቸው የአእምሮ ጤና እክል በፀሎት እና በፀበል እንጂ የረባ አገልግሎት የሚያገኙበት አሰራር እንደሌለ ዳይሬክተሩ ነግረዉናል።

በተለይም ገጠራማዉ ክፍል የስነ አእምሮ ድጋፍ እና ህክምና ስለ አለመኖሩ ÷ መገለሎችም እንዳሉ ተነግሯል።

በዚህም ወጣቶቹ እምነትን በበለጠ እየመረጡ እንዳለ ተገልጿል። ጦርነቱ በወንዶች ላይ የስራ አጥነት ÷ የሱስ÷ ድብርት በሴቶች ደግሞ ወሲባዊ ጥቃት ከአጋላጮቹ ዉስጥ ሆነዉ የተገኙ መሆናቸው ጥናቱ አመላክቷል።

ከዚህ በተጨማሪም በነበረዉ ንፅፅር ያለ እድሜ ጋብቻ መቀነሱን ያሳየ ቢሆንም በጥናቱ ክትትል ሲደረግባቸዉ ከነበሩት አንድ አምስተኛው ያህሉ ከ18 አመት በታች የሆኑት ማግባታቸዉን አሳይቷል።

ይህ በ8 ነጥቦች ላይ ክትትል እያደረገ የቆየዉ ጥናት በተለይም የህፃናት መቀንጨር ዙሪያ ሲያደርግ በቆየዉ ክትትል አሁን በአገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበረ ላለዉ ብሄራዊዉ የትምህርት ቤት ህፃናት ምገባ ግፊት ሲያደርግ የቆየ መሆኑን ዶ/ር አሉላ ፓንክረስት ገልፀዋል።

የተደረጉት 8 ያህል የክትትል ነጥቦች ምክረ ሀሳብ ተካቶባቸዉ ለፓሊሲ ግብአት እንዲዉል ለምክክር በትናንትናው እለት ቀርቧል።

ኢትዩጵያን ጨምሮ በአራት የተለያዩ ሀገራት ተመሳሳይ ጥናት ከኦክስፎርድ ዩንቨርሲቲ ጋር በመተባበር እየተደረገ መሆኑንም ሰምተናል።

ስደት÷ ትምህርት÷ የምግብ ዋስትና÷ አካል ጉዳተኛነት÷ የስነ ተዋልዶ ጤና እና ሌሎች የጥናቱ ነጥቦች መሆናቸዉ ተገልፆል።

ቁምነገር አየለ

ጥር 22/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *