በከፍተኛ ወጭና በብዙ ትጋት ለሕዝብ አገልግሎት እንዲውሉ የተገነቡ የስፖርት ሜዳዎች በአግባቡ ለሕዝብ ተደራሽ እየሆኑ እንዳልሆነና ለብልሹ አሰራር ተጋልጠው እንደሚገኙ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።
በቅርቡ በተካሄደ የአመራሮች ግምገማ ላይ እንደተገለጸዉ፤ በተለይ በየአካባቢው የተገነቡ የስፖርት ሜዳዎች ታጥሮባቸዋል በሚል የሕዝብ ቅሬታ እየቀረበባቸው ይገኛል።
ስፖርት ቢሮው እነዚህን ሜዳዎች ለሕዝብ ክፍት ከማድረግ ይልቅ፣ በግልፅነት ላይ የተመሰረተ አሰራር ባለመከተሉና ለታችኛው መዋቅር መመሪያዎችን ባለማውረዱ በከንቲባዋ አማካኝነት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል።
ካቢኔው የስፖርት ሜዳዎችን ለማስተዳደር የሚረዱ ትንንሽ ክፍያዎችንና አጠቃቀሞችን የሚወስን መመሪያ ቢያወጣም፤ በታችኛው መዋቅር “አልደረሰንም” በሚል ሰበብ ለሕዝብ አገልግሎት እንዳይሰጡ መሰናክል እየተፈጠረ መሆኑ ተረጋግጧል።
ሜዳዎቹ ለሕዝብ በነፃ ወይም በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረብ ሲገባቸው አላስፈላጊ ክፍያ እንደሚጠየቅባቸውናበደላሎች አማካኝነት አገልግሎቱ እየተስተጓጎለ መሆኑን እንደሚያውቁ ከንቲባዋ ገልፀዋል።
አመራሩ በቁርጠኝነት ወደ ታች ወርዶ ችግሩን ካልፈታና ግልፅነትን ካላሰፈነ፤የሪፎርም ስራው የተሟላ እንደማይሆን ተመላክቷል።
በመሆኑም የስፖርት ቢሮውና የሚመለከታቸው አካላት በ15 ቀንና በአንድ ወር ውስጥ ተገንብተው ያለቁ ሜዳዎችን ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ፣ የክትትልና የቁጥጥር ስራቸውን በአፋጣኝ እንዲያጠናክር ታዘዋል።
ሊዲያ ደሳለኝ
ጥር 22/2018 ዓ.ም
