የአርሰናሉ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ፕሪምየር ሊጉ ቡድኖች በጨዋታ ለት ስኳዳቸው የሚይዟቸውን ተጫዋቾች ቁጥር ከ 20 ወድ 23 ከፍ እንዲያደርግ ጠይቋል።
ይህንን ማድረግ “የተጫዋቾችን ዋጋ እና የአእምሮ ጤና” ለመጠበቅ ያግዛል የሚል ዕምነት አለው።
ፕሪምየር ሊጉ በዚህ ወቅት የሚፈቅደው ክለቦች በጨዋታ ዕለት ዘጠኝ ተጫዋቾችን ብቻ በተጠባባቂነት እንዲይዙ ነው። ከእነዚህ መካከል አምስቱን በጨዋታ ቀይረው ማስገባት ይችላሉ። የጭንቅላት ጉዳት ያጋጠመው ተጫዋች ሲኖር ብቻ ተጨማሪ ቅያሪ መፈጸም ይፈቀድላቸዋል።
አርቴታ የጨዋታ ዕለት ስኳድ ከዚህም በላይ ሰፊ ሊሆን ይገባል የሚለውን መከራከሪያውን ያቀረበው በአስገዳጁ ህግ ምክንያት ከጨዋታ ዕለት ስኳድ ውጪ የሚደረጉ ነገር ግን ደረጃቸው ከፍ ያሉ ተጫዋቾች መኖራቸውን በመግለጽ ነው። እንደ ክርስቲያን ኖርጋርድ ያሉ ተጫዋቾችን በምሳሌነት ጠቅሷል።
ፕሪምየር ሊጉ የቻምፒየንስ ሊግን ፈለግ ይከተላል የሚል ተስፋ እንዳለውም ገልጿል። በቻምፒየንስ ሊግ ተቀያሪ ግብጠባቂን ጨምሮ 23 ተጫዋቾችን በጨዋታ ዕለት ስኳድ መያዝ ይፈቅዳል።
“በዚህ ወቅት ምንም ማድረግ ስለማንችል ከጨዋታ ዕለት ስኳድ ውጪ የምናደርጋቸው ሁለትና ሶስት ተጫዋቾች ይኖራሉ። ይህንን እኔ መለወጥ አልችልም። የፕሪምየርሊጉ ደንብ አያፈናፍነኝም። ምናልባት ፕሪምየር ሊጉ ከሚቀጥለው የውድድር ዘመን ጀምሮ ከግብጠባቂዎች ውጪ በስኳዱ ውስጥ የምንይዛቸውን ተጫዋቾች ቁጥር ከ17 ወደ 18 ከፍ ያደርገው ይሆናል” ብሏል።
“ደንቡ ይሻሻል እንጂ ለሆቴል፣ ለጉዞ እና ሌሎች ጉዳዮች የምናወጣውን ተጨማሪ ወጪ አያስጨንቀንም” ብሏል።
አቤል ጀቤሳ
ጥር 22/2018 ዓ.ም
