በ6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በህዳሴ ግደቡ ግንባታ ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት እርዳታም ሆነ ብድር አለመውሰዷን ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ለግድቡ ማን እንደከፈለ ታውቃላችሁ? ዩናይትድ ስቴትስ” ሲሉ በዋይት ሐውስ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ስልጣን የመጡበትን አንደኛ አመት አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡
በዛሬው ዕለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታዲያ ”በህዳሴ ላይ አንድም ብር እርዳታ፣ አንድም ብር ብድር ኢትዮጵያ አልወሰደችም” ብለዋል፡፡
”በጀግኖች ኢትዮጵያውያን ቁርጠኛ አቋም በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጭም ያሉ ኢትዮጵያውያን በቁርጠኝነት ጨክነው በጋራ ቆመው ስለሰሩ የተከወነ ፕሮጀክት ነው” ሲሉም አክለዋል::
”ህዳሴን ካለ አንድ ብር እርዳታ፣ ካለ አንድ ብር ብድር ያሳካ መንግስት ፕሮጀክት አይሰራም ሊባል አይችልም ግፍ ነው” ሲሉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌሎች ትልልቅ ፕሮጀክቶችም እየተከናወኑ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
አዲስአለም አበበ
ጥር 26/2018 ዓ.ም
