ሰኞ ምሽት ሩሲያ በዩክሬን የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ላይ የፈጸመችው ጥቃት ‹‹አረመኔያዊ›› እና ‹‹ፍፁም ነውር››ነው ሲሉ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኬር ስታርመር ገልጸዋል።
ጠቅላዩ ይህንን አስተያየት የሰጡት ሩሲያ በዋና ከተማዋ ኪቭ እና በሌሎች ቦታዎች በሚገኙ የኃይል ማመንጫዎች እና ወሳኝ መሰረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ከሰነዘረች ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ነው።
ጥቃቱ የተፈጸመው በዩክሬን ብርቱ ቅዝቃዜ በሰፈነበት ወቅት እና ትራምፕ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እንዲያከብሩት ጠይቀውት የነበረው የአንድ ሳምንት የተኩስ ማቆም ስምምነት ካበቃ በኋላ ነው።
ትራምፕ እንደተናገሩት ፑቲን ቃላቸውን ጠብቀዋል፤ በተጨማሪም ጦርነቱ እንዲቆም እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
በጥቃቱ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ሲሆን፤ በኪቭ ከ1 ሺህ በላይ የመኖሪያ ሕንጻዎች ያለ ሙቀት አቅራቢ የቀሩ ሲሆን፤ በምስራቃዊቷ የካርኪቭ ከተማ የሚገኝ አንድ የኃይል ማመንጫ ደግሞ ለጥገና በማይመች መልኩ መውደሙ ተነግሯል።
ነዋሪዎች ሌሊቱን በሜትሮ ጣቢያዎች ውስጥ ለመጠለል ሲገደዱ፤ አንዳንዶች ከከፍተኛ ቅዝቃዜ ለመከላከል በጣቢያዎቹ ውስጥ ድንኳን ዘርግተዋል።
ባለስልጣናት የከተማዋ ነዋሪዎች ሙቀት እንዲያገኙ በኪቭ ዙሪያ ማዕከላት በማቋቋም ላይ ናቸው ሲል ቢቢሲ ነው የዘገበው።
ሀና ሰይፉ
ጥር 27/2018 ዓ.ም
