አምባገነኑ የእግር ኳስ ሰው

አል-ሳዲ ጋዳፊ የቀድሞው የሊቢያ ፕሬዝዳንት የነበሩት ሙአመር ጋዳፊ ልጅ ነው፡፡ ከልጆቻቸው በሙሉ ነውጠኛ እና አምባገነን መሆኑ ይነገርለታል፡፡

ብቸኛው መልካም ባህሪው ተደርጎ የሚወሰድለት ነገር ቢኖር ለእግር ኳስ ያለው ፍቅር ብቻ ነው፡፡ እንደዛም ቢሆን ግን ይህ አምባገነን ባህሪው በእግር ኳሱ ውስጥ በነበረው ቆይታም በሰፊው ይንፀባረቅ ነበር፡፡

አል-ሳዲ ጋዳፊ በሊቢያ እግር ኳስ ውስጥ በነበረው ተፅዕኖ ይታወቃል። ኳስ ከመጫወት አልፎ ራሱን የሀገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትም አድርጎ ሾሞ ነበር፡፡ በወቅቱ ታዲያ የፌዴሬሽኑ ህጎች ለእሱ በሚያደላ መልኩ እንዲዘጋጁ አድርጓቸዋል።

እግር ኳስ መጫወት የጀመረው እ.ኤ.አ በ2000 ለታዋቂው የሀገሪቱ ክለብ አል-አህሊ ትሪፖሊ በመፈረም ነበር፡፡ ፊርማው ሳይደርቅም አንድ ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡ ይህም “ጋዳፊ ከሚለው የእኔ ስም ውጪ የማንኛውም ተጨዋች ስም በማሊያው ጀርባ ላይ እንዳይፃፍ” የሚል ነበር፡፡

በዚህም መሰረት ሌሎቹ ተጫዋቾች ቁጥራቸው ብቻ ነበር የሚፃፈው። ይህም ብቻ ሳይሆን ተጨዋቾች ተቀይረው በሚገቡበትም ሆነ በሚወጡበት ሰዓት ቁጥራቸው ብቻ እንጂ ስማቸው አይጠራም ነበር፡፡

ዳኞች ለጋዳፊ ክለብ ያደሉ ነበር፤ ተቃውሞ የሚያሰሙ ደጋፊዎችንና ተጨዋቾችንም የፀጥታ ኃይሎች አፍነው በመውሰድ ዝም ያሰኟቸው ነበር።

አል-ሳዲ ጋዳፊ ከሊቢያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትነቱ ባሻገር ራሱን የሊቢያ ብሔራዊ ቡድንና የአል-አህሊ ትሪፖሊ ክለብ አምበል አድርጎ ሾሞ ነበር። በዚህ ክለብ ውስጥ አንድ ዓመት ከቆየ በኋላ ወደ ማልታው ቢርኪርካራ ክለብ ለማምራት ያደረገው ሙከራ ባለመሳካቱ በ2001 ወደሌላኛው የሀገሪቱ ክለብ አል-ኢትሃድ ትሪፖሊ አመራ፡፡ በዛ እስከ 2003 ከቆየ በኋላ ወደ አውሮፓ ተሻግሮ የጣልያኑን ፔሩጂያ ተቀላቀለ፡፡

አል-ሳዲ ፔሩጂያን የተቀላቀለው ክለቡ የፋይናንስ ችግር አጋጥሞት ስለነበር “እኔ ገንዘብ ልስጣችሁ፤ እናንተ ደግሞ አስፈርሙኝ” ብሎ ተደራድሮ ነበር፡፡ የተወሰነ የባለቤትነት ድርሻም ነበረው፡፡ እዛ እንደደረሰም ዲዬጎ ማራዶናን ቴክኒክ አማካሪ፤ ካናዳዊውን የቀድሞውን የአጭር ርቀት ዝነኛ አትሌት ቤን ጆንሰንን ደግሞ የግል አሰልጣኙ አድርጎ ቀጥሮት ነበር።

እንደዛም ቢሆን በፔሩጂያ በነበረው ቆይታ ከጁቬንቱስ ጋር በተደረገ አንድ ጨዋታ ላይ ብቻ ነው የተሰለፈው፤ እሱንም ተቀይሮ ገብቶ ነው የተጫወተው።

ከጨዋታው በኋላ በተደረገለት ምርመራ “ናንድሮሎን” (Nandrolone) የተባለ አበረታች ንጥረ ነገር በደሙ ውስጥ በመገኘቱ ለአንድ ዓመት ከእግር ኳስ ታግዷል።

አል-ሳዲ የአጥቂ ስፍራ ተጨዋች የነበረ ቢሆንም ፈጣን ግን አልነበረም፡፡ እንደውም ላ ሪፐብሊካ የተባለው ታዋቂው የጣልያን ጋዜጣ ስለዚሁ ጉዳይ ባወጣው አንድ ዘገባ “አሁን ካለው ፍጥነት በሁለት እጥፍ ቢፈጥን እንኳ፤ አሁንም በጣም ቀርፋፋ ከሚባሉት ራሱ በሁለት እጥፍ የዘገየ ነው” ብሎ ነበር። በዚህ የተበሳጨው የሙአመር ጋዳፊ ልጅ ታዲያ የጋዜጣው ድረ-ገፅ በሊቢያ ምድር እንዳይነበበ አሳግዶታል፡፡

አምባገነኑ አል-ሳዲ እ.ኤ.አ. በ2005/06 ሌላኛውን የጣልያን ክለብ ዩዲኔዜን ተቀላቅሎ ከካግሊያሪ ጋር በነበረ ጨዋታ ለ10 ደቂቃ ብቻ ተጫውቷል። በ2006/07 ደግሞ ሳምፕዶሪያን ቢቀላቀልም አንድም ጨዋታ ሳይጫወት ቀርቷል።

አሁን የ52 ዓመት ጎልማሳ የሆነው አል-ሳዲ ጋዳፊ እጅግ ሲበዛ አምባገነን ነበር፡፡ ባለትዳር ቢሆንም ከተመሳሳይ ፆታ ጋርም ግንኙነት ይፈፅም እንደነበር ይነገራል፡፡ እንደውም የሊቢያው የእርስ በርስ ጦርነት ካበቃ በኋላ በአል-አህሊ ትሪፖሊ ክለብ ውስጥ አብሮት ይጫወት የነበረው ሬዳ ሚላድ አል ታዋርጊ የተባለው ተጨዋች በሰጠው አስተያየት አምባገነኑ ያቀረበለትን የወሲብ ጥያቄ ባለመቀበሉ ለሁለት ዓመት ተኩል ወደ እስር ቤት እንደላከው ገልጿል፡፡

አባቱ ሙአመር ጋዳፊ ከስልጣን ወርደው ከተገደሉ በኋላ አምባገነኑ ልጃቸው አል-ሳዲ ጋዳፊ በተቃዋሚዎች ቁጥጥር ስር ውሎ መከራውን አይቷል፡፡ በስተመጨረሻም ከእስር ከተለቀቀ በኋላ በስደት ቱርክ ገብቷል፡፡ ይሁንና ሀገሪቷ “እኔ ጋር የለም” ስትል ብታስተባብልም እስከ 2023 ድረስ ግን በኢስታንቡል ይኖር እንደነበር ተረጋግጧል፡፡ አሁን ግን የት እንዳለ አይታወቅም፡፡

ምስጋናው ታደሰ

ጥር 27/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *