የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሊቀ-መንበር ግርማ ዋቄ የዩጋንዳ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው መሾማቸውን አንድ ከፍተኛ የሀገሪቱ ባለሥልጣን ገለጹ። 

አቶ ግርማ አየር መንገዱን እንዲመሩ መሾማቸው የተገለጸው ትላንት ረቡዕ የዩጋንዳ ፕሬዝደንት ዬዌሪ ሙሴቬኒ ጋር ከተገናኙ በኋላ ነው።

የ81 ዓመቱ ሙሴቬኒ በዩጋንዳ ብሔራዊ ቤተ-መንግሥት ከአቶ ግርማ ጋር ትላንት ረቡዕ ሲገናኙ አየር ትራንስፖርትን በተመለከተ መነጋገራቸውን ገልጸዋል።

የዩጋንዳ የወጣቶች እና ሕጻናት ጉዳዮች ሚኒስትር ባላም ባሩግሐራ በተረጋገጠ የኤክስ (X) ገጻቸው ባሠፈሩት መልዕክት ፕሬዝደንት ሙሴቬኒ አቶ ግርማን የዩጋንዳ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አድርገው እንደሾሙ አስታውቀዋል።

ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው አቶ ግርማ የተሾሙት የፕሬዝደንቱ ልጅ እና የዩጋንዳ ጦር አዛዥ በሆኑት ሙኾዚ ካይኔሩጋባ ጥቆማ እንደሆነ ገልጸዋል።

የዩጋንዳ አየር መንገድ እስካሁን ድረስ በይፋ ያለው ነገር የለም።

አቶ ግርማ ለዩጋንዳ አየር መንገድ አዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እስኪሾም ድረስ ባለው የሽግግር ጊዜ ተቋሙን ይመራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የዩጋንዳ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት ጀኒፈር ባሙቱራቺ ከኃላፊነታቸው የለቀቁት በዚህ ሳምንት ነበር። አየር መንገዱ አዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለመቅጠር የመቅጠር ማስታወቂያ ማውጣቱ ይታወሳል ብሏል የጀርመን ድምፅ ።

የ82 ዓመቱ አቶ ግርማ የኢትዮጵያ አየር መንገድን በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግለዋል።

ከመጋቢት 2014 እስከ ሰኔ 2015 የአየር መንገዱ ግሩፕ የቦርድ ሊቀ-መንበር ነበሩ። አቶ ግርማን በቦርድ ሊቀ-መንበርነት የተኳቸው የኢትዮጵያ አየር ኃይል አዛዥ ሉቴናንት ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ናቸው።

ጥር 28/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *