የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደንበኞች ቁጥሩ ከ 5.46 ሚሊየን በላይ መድረሱን ገለፀ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የ2018 አ.ም የስድስት ወር የእቅድ አፈፃፀሙን በትናንትናዉ እለት ለመገናኛ ብዙሃን ገልጿል።

ባለፉት 6 ወራት ኤሌክትሪክ የተገናኘላቸው ደንበኞች ጨምሮ አጠቃላይ የደንበኞች ቁጥር 5.46 ሚሊዮን በላይ መሻገሩን ገልፆል።

1.1 ሚሊዮን የኢነርጂ ቆጣሪዎችን ቤት ለቤት ለመመርመር አቅዶ 1.29 ሚሊዮን መመርመር እንደቻለ የገለፀዉ አገልግሎቱ በምርመራው 39 ሺህ 704 ግኝቶች ተገኝተው የማስተካከያ እርምጃ እንደተወሰደም ተገልጿል።

መግለጫውን የሰጡት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢ/ር ጌቱ ገረመዉ፤ከኢነርጂ ሽያጭ ከተሰበሰበው 34.3 ቢሊዮን ብር ገቢ ውስጥ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል 20.5 ቢሊዮን ብር ለኢነርጂ ግዥ ክፍያ መፈፀሙን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የተጠያቂነትን ስርዓት ለማስፈን ባከናወነው ሥራ 651 አመራርና ሠራተኞች ላይ እርምጃ መውሰዱን ከመድረኩ ሰምተናል።

የኤሌክትሪክ ኃይል ስርቆት የፈፀሙ 18 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመስርቶ 2ሺህ ብር መቀጮ እና 2.95 ሚሊዮን ብር እንዲከፍሉ ስለመደረጉ በተገለፀበት መድረክ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ስርቆት እና ውድመት ባደረሱ 14 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመስርቶ ከ2 ሺህ ብር መቀጮ ጀምሮ እስከ 10 ዓመት ፅኑ እስራት ድረስ እንዲቀጡ በፍርድ ቤት ስለመወሰኑም ተገልጿል።

በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወር ከኢነርጂ ሽያጭ፣ ከአዲስ ደንበኛ መስተንግዶ፣ ከማያገለገሉ ንብረቶች ሽያጭና ከልዩ ልዩ ገቢ 52.26 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል ተብሏል።

ቁምነገር አየለ

ጥር 29/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *