አትሌቱ በፓሪስ ኦሎምፒክ 5ኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ የAthletics Integrity Unit ኬንያዊውን የረጅም ርቀት ሯጭ ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት በማንኛውም ውድድር ላይ እንዳይሳተፍ እገዳ ጥሎበታል።
ቅጣቱም ከሰኔ 10/2025 እስከ ሰኔ 9/2029 ድረስ ተፈፃሚ ይሆንበታል፡፡ ከሰኔ 10/2025 ወደዚህ ያስመዘገባቸው ውጤቶቹ የሚሰረዙ ሲሆን፤ ያገኛቸውን የገንዘብ ሽልማቶችም ይነጠቃል፡፡
እገዳው የተጣለበት በአትሌት ባዮሎጂካል ፓስፖርቱ (ABP) ላይ ልዩነቶች ወይም ግድፈቶች በመገኘታቸው ነው። ይህ የባዮሎጂካል ፓስፖርት ዘዴ አትሌቶች አቅምን የሚያሳድጉ አበረታች ንጥረ ነገሮችን (performance-enhancing drugs) መጠቀማቸውን በተዘዋዋሪ መንገድ ለመከታተል የሚያገለግል የክትትል ስልት ነው።
የ26 ዓመቱ ኬንያዊ በፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ በወንዶች 10,000 ሜትር ፍጻሜ 26:43.98 በሆነ ሰዓት 5ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቆ ነበር። ይሁንና የAthletics Integrity Unit ይህ ውጤቱ ተቀባይነት አጥቶ እንደሚሰረዝ አስታውቋል።
ኮኤች ባለፈው ሰኔ ወር ላይ በጊዜያዊነት ሲታገድ በወንዶች 10,000 ሜትር በዓለም 6ኛ ደረጃ ላይ የነበረ ሲሆን፤ በ10 ማይል (16.09 ኪ.ሜ) ርቀት ደግሞ 44:02 በሆነ ሰዓት የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤትም ነበር።
ባለፉት ሁለት ታላላቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ፍጻሜ ላይ የደረሰ ሲሆን፤ በፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ እና በ2023 በቡዳፔስት በተካሄደው የዓለም ሻምፒዮና በሁለቱም የ10,000 ሜትር ውድድሮች 5ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
በቡዳፔስት ከካናዳዊው ሞ አህመድ በአንድ ደረጃ ቀድሞ የነበረ ሲሆን፤ በፓሪስ ደግሞ ከአህመድ በአንድ ደረጃ ዝቅ ብሎ አጠናቆ ነበር።
ባለፉት አምስት ዓመታት ኮኤች 23 ጊዜ ምርመራ የተደረገለት ቢሆንም Athletics Integrity Unit እ.ኤ.አ በ2024 የኬንያ የኦሎምፒክ ማጣሪያ እና በፓሪስ ኦሎምፒክ አካባቢ ከተሰበሰቡት ናሙናዎች ውስጥ በሄሞግሎቢን መጠኑ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ አግኝቷል።
የእሱ ባዮሎጂካል ፓስፖርት (ABP) አጠራጣሪ ሆኖ በመገኘቱ ለባለሙያዎች ቡድን የቀረበ ሲሆን፤ ቡድኑም በዚህ ወቅት በተሰበሰቡት የደም ናሙናዎች ላይ ያልተለመዱ ግኝቶችን አረጋግጧል።
ባለሙያዎቹ ባደረጉት ግምገማ፣ የታየው ከፍተኛ የሄሞግሎቢን መጠን ኪቤት የደም ዶፒንግ (blood doping) ሳይጠቀም እንዳልቀረ የሚያሳይ ከፍተኛ እድል እንዳለ ደምድመዋል።
የባዮሎጂካል ፓስፖርት (ABP) ዓላማ የአንድን አትሌት ባዮሎጂካዊ ምልክቶች በጊዜ ሂደት በመከታተል፣ ዶፒንግን ሊያመለክቱ የሚችሉ መደበኛ ያልሆኑ ለውጦችን ለይቶ ማውጣት ነው።
ኮኤች እና የሕግ ቡድኑ በፓስፖርቱ ላይ የታዩት ያልተለመዱ ግኝቶች በኮቪድ-19 (COVID-19) ወቅት በአፍ የሚወሰድ የአይረን ንጥረ ነገር ማሟያ እና በከፍታ ቦታዎች ላይ በሚደረግ ልምምድ ምክንያት የመጡ ናቸው ሲሉ ተከራክረዋል።
የኪቤት ቡድን ለክርክሩ እንደ ማጠናከሪያ የኖራ ጄሩቶን ጉዳይ የጠቀሰ ሲሆን፣ በእሷ ጉዳይ ወቅት ኮቪድ ለውጤቱ መዛባት እንደ አንድ ምክንያት ተቀባይነት አግኝቶ ነበር።
ኮኤች በዶፒንግ ምክንያት እገዳ እየተጣለባቸው ባሉ ታዋቂ ኬንያውያን አትሌቶች ዝርዝር ውስጥ የቅርብ ጊዜው ተመዝጋቢ ሆኗል።
በአሁኑ ወቅት በAIU ዓለም አቀፍ የእገዳ ዝርዝር (Global List of Ineligible Persons) ላይ ከ1መቶ50 በላይ ኬንያውያን አትሌቶች በዶፒንግ ምክንያት እገዳ ተጥሎባቸው ይገኛሉ።
ምስጋናው ታደሰ
ጥር 29/2018 ዓ.ም
