የሀገራችን የቱሪዝም እና መስተንግዶ ዘርፍ ግንባር ቀደም አምባሳደር፣ ‹‹የውብ ሀገር›› ፕሮግራም መስራች የሆነው ታታሪው ጋዜጠኛ ዘሪሁን ግርማ ትናንት ከሰዓት በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለከቱት ጋዜጠኛ ዘሪሁን ትናንት ረፋድ ስራውን አከናውኖ ወደ ቤቱ ተመልሶ የነበረ ቢሆንም በዕለቱ 5ኛ ፎቅ ላይ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ለመግባት ደረጃውን እየወጣ ሳለ 3ኛ ፎቅ ላይ ሲደርስ በድንገት መንቀሳቀስ እንዳቃተው እና ለልጁ ደውሎ ‹‹ቶሎ ድረሺልኝ፣ አቅቶኛል›› በማለት ጥሪ በማድረጉ ጎረቤቶች ተሰባስበው ወደ ሆስፒታል ቢወስዱትም ህይወቱን መታደግ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
ጋዜጠኛ ዘሪሁን ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያን ባህል እና ቱሪዝም ለማስተዋወቅ በታታሪነት ሲያገለግል ቆይቷል፡፡
በጋዜጠኝነት ሙያው ለረጅም ዓመታት የሀገራችንን ባህል፣ የቱሪስት መስህቦች ከማስተዋወቅ ባለፈ ለባህልና ለጥበባት ዘርፍ ዕድገትም የነበረው ፍቅር ወደር የለሽ ነበር፡፡
ጋዜጠኛ ዘሪሁን የኢትዮጵያ ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማኅበር መስራች እና የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የባህልና ኪነ-ጥበባት ጋዜጠኞች ፎረም መሪም ነበር።
በኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ሬዲዮ በሳምንት ለሁለት ቀናት ‹‹ኢትዮ ቱሪዝም›› የተሰኘ በቱሪዝም ላይ ትኩረት ያደረገ ፕሮግራም ሲሰራም ቆይቷል፡፡
በተጨማሪም በዛሚ 90.7፣ በደቡብ ኤፍ ኤም 100.9 እና በ‹‹ውብ ሀገር›› ዩቲዩብ ቻናሉ የማይረሱ ስራዎችን ለአድማጭ ተመልካቾች ያደርስ ነበር ፡፡
ባለትዳር እና የ2 ልጆች አባት የነበረው ዘሪሁን የመጨረሻ ስራውን ወደ ከፋ በማምራት መድሃኔዓለም ቤተክርስቲያንን በተመለከተ ዝግጅት የሰራ ሲሆን፤ ይህንኑም ዝግጅት ከ3 ቀናት በፊት በፌስቡክ ገፁ ላይ አጋርቷል።
የጋዜጠኛ ዘሪሁን ስርዓተ ቀብር በትውልድ ከተማው አርባምንጭ እንደሚፈጸም ታውቋል፡፡ በዚህም ምክንያት የጋዜጠኛ ዘሪሁን አስከሬን ወላጆቹ ወደሚገኙበት አርባ ምንጭ ከተማ ተሸኝቷል።
ኤፍኤም 107.8 ስለቱሪዝም ተናግሮ በማይጠግበው ዘሪሁን ግርማ ድንገተኛ ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን በመግለጽ ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጅ ዘመዶቹና ለሙያ ባልደረቦቹ መጽናናትን ይመኛል፡፡
ሀና ሰይፉ
ጥር 29/2018 ዓ.ም
