በሞስኮ የሚገኘው የኒውሮ-ቴክኖሎጂ ኩባንያ ኒሪ፤ በአዕምሮ ውስጥ በሚተከል የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያ አማካኝነት እርግቦችን ከርቀት መቆጣጠር የሚያስችል አዲስ የፈጠራ ሥራ መሥራቱን ገልጿል።
ይህ ቴክኖሎጂ ትናንሽ ኤሌክትሮዶችን በወፎቹ የራስ ቅል በኩል ወደ አዕምሮአቸው በማስገባትና በጀርባቸው ላይ ከሚታሰር የፀሐይ ኃይል መቆጣጠሪያ ጋር በማገናኘት ፤ ወፎቹ ወደ ግራና ቀኝ እንዲታጠፉ የኤሌክትሪክ ትዕዛዝ የሚሰጥ ነው።
ኩባንያው ሰው ሰራሽ ድሮኖችን ከመጠቀም ይልቅ እርግቦችን መምረጡ ወፎቹ ባትሪ ሳይፈልጉ በቀን እስከ 4መቶ80 ኪሎ ሜትር መብረር የሚችሉ በመሆናቸውና ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግባቸውን የአየር ክልሎች ሰብረው መግባት ስለሚችሉ እንደሆነ አስታውቋል።
እነዚህ ‹‹ሳይቦርግ እርግቦች›› ለስለላ የሚያገለግል ካሜራና የGPS መገኛ የተገጠመላቸው ሲሆን፤ ኩባንያው ወደፊት ቁራዎችንና ሌሎች የባሕር ወፎችንም ለተመሳሳይ ተግባር ለማሰማራት አቅጃለሁ ብሏል።
ምንም እንኳን ተቋሙ ቴክኖሎጂው ለነፍስ አድንና ለኢንዱስትሪ ቁጥጥር ይውላል ቢልም ባለሙያዎች ግን የሩሲያ መንግሥት ለድብቅ ስለላና ለጦርነት ተግባር ሊጠቀምበት ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት አላቸው ሲል ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል።
ሐመረ ፍሬዉ
የካቲት 03/2018 ዓ.ም
