የቡርኪና ፋሶ የሽግግር ፓርላማ ሰኞ ዕለት ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያግድ ረቂቅ አዋጅ አፅድቋል።
ይህ እርምጃ በካፒቴን ኢብራሂም ትራኦሬ የሚመራው ወታደራዊ ጁንታ ቁጥጥሩን ለማጠናከር ያስችለዋል ሲሉ ታዛቢዎች ገልጸዋል።
በሕግ አውጪዎች ምንም ዓይነት ተቃውሞ ያልገጠመው ይህ የሕግ ጽሑፍ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ቻርተር እንዲሁም የፓርቲዎችን ፋይናንስ፣ የምርጫ ቅስቀሳ እና የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን ሁኔታ የሚመለከቱ ሕጎችን ይሽራል።
በ2022 ጦር ኃይሉ ሥልጣን ከተቆጣጠረ ወዲህ በዚህ የሳህል አገር የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ታግዶ ቆይቷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመብት ሃላፊ የቡርኪናፋሶ መንግስት በሲቪክ ምህዳር ላይ የሚደርሰውን ጭቆና እንዲያቆም እና ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች የመከልከል እቅዱን እንዲሽር ጠይቀዋል።
በሐምሌ ወር የቡርኪና ፋሶ ባለሥልጣናት በመደራጀት ነፃነት ላይ አዲስ ገዳቢ ሕግ ያወጡ ሲሆን፣ በኅዳር ወር ደግሞ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ማኅበራት የገንዘብ ሂሳባቸውን በመንግሥት በሚተዳደር ባንክ ብቻ እንዲከፍቱና እንዲያንቀሳቅሱ የሚያዝ አዲስ አዋጅ አውጥተዋል ሲል የዘገበዉ አፍሪካ ኒዉስ ነዉ።
ሊዲያ ደሳለኝ
የካቲት 04/2018 ዓ.ም
