አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን ዳግም የምታጸናበት ሳምንት

የካቲት 4 ቀን 2018 ዓ.ም መዲናችን አዲስ አበባ የአፍሪካ መሪዎችን እና ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶችን በታላቅ ዝግጅት በመቀበል ጀምራለች።

ይህ ሳምንት በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ ደማቅ አሻራ የሚያሳርፍ ነው፤ ምክንያቱም አገሪቱ 39ኛውን የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤን ብቻ ሳይሆን፣ ከኅብረቱ ጉባኤ ጎን ለጎን የሚካሄደውን 2ኛውን የጣሊያን-አፍሪካ ስብሰባንም በጋራ ታስተናግዳለች።

የጉባኤዎቹ መርሐ-ግብር ምን ይመስላል?
የዘንድሮው ስብሰባ በደረጃ የተከፋፈለ ሲሆን፣ ዋና ዋናዎቹ ክንውኖች የሚከተሉት ናቸው
የካቲት 4 – 5 48ኛው የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት (የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች) ስብሰባ።
የካቲት 6 ታሪካዊው የጣሊያን-አፍሪካ የመሪዎች ስብሰባ በአዲስ አበባ።
የካቲት 7 – 8 39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ (AU Assembly)።

የዘንድሮው ትኩረት፡ ‹‹ውሃ ለሕይወትና ለልማት››
የ2026 የኅብረቱ መሪ ቃል ‹‹ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት››የሚል ነው።
አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ እና በውሃ እጥረት እየተፈተነች ባለችበት በዚህ ወቅት፣ ይህ አጀንዳ ለአህጉሪቱ የምግብ ዋስትና እና የኢንዱስትሪ እድገት ወሳኝ መሆኑ ይታመናል።
ኢትዮጵያ ይህንን መሪ ቃል ከራሷ ‹‹የአረንጓዴ አሻራ›› እና ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ስኬቶች ጋር በማስተሳሰር፣ አህጉራዊ የውሃ ትብብርን ለማጠናከር እንደ መልካም አጋጣሚ ትጠቀምበታለች።

ኢትዮጵያና ‹‹ስንዱነቷ››
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በሎጅስቲክስ፣ በፕሮቶኮል እና በጸጥታ ረገድ ዝግጅቷን አጠናቃለች።
የኮሪደር ልማት ውጤት፤ ከተማዋን የማስዋብ እና የመንገድ መሰረተ ልማቶችን የማዘመን ስራ እንግዶችን ለመቀበል ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
የበጎ ፈቃደኝነት ባህል-1መቶ79 ወጣት በጎ ፈቃደኞች ልዑካኑን በቆየው የኢትዮጵያ የእንግዳ ተቀባይነት ባህል እንዲያገለግሉ ተሰማርተዋል። ይህ ደግሞ ‹‹ዜጋ ዲፕሎማሲን›› ለማጠናከር የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) አስተሳሰብ አንዱ አካል ነው።

ለከተማዋ ነዋሪዎችና ለእንግዶች የተላለፈ መልዕክት
ጉባኤው እጅግ ሰፊ በመሆኑ፣ በመዲናዋ የሚከተሉት ነጥቦች ትኩረት ይሻሉ
የትራፊክ ፍሰት፦ በቦሌ አየር መንገድ፣ በሳር ቤት (AU)፣ በዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም እና በዋና ዋና ሆቴሎች አካባቢ መንገዶች ለጊዜው ሊዘጉ ስለሚችሉ አማራጭ መንገዶችን መጠቀም ይመከራል።
ጸጥታ፦ ከፍተኛ የደህንነት ጥበቃ የሚደረግ በመሆኑ፣ ነዋሪዎች የተለመደውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።

ይህ ጉባኤ ለኢትዮጵያ የ‹‹ኮንፈረንስ ቱሪዝም››ትልቅ እድል ከመሆኑም በላይ፣ አዲስ አበባ የአፍሪካ የፖለቲካ ዋና ከተማ መሆኗን ለዓለም የምታሳይበት ወርቃማ ወቅት ነው።
አህጉራዊ አንድነትንና የኢኮኖሚ ትስስርን የሚያጠናክሩ ውሳኔዎች ከዚህ መድረክ እንደሚወጡ ይጠበቃል።

ለዓለም አሰፋ

የካቲት 04/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *