የኮሎምቢያው ፕሬዝዳንት ጉስታቮ ፔትሮ የግድያ ሙከራ እንደተሰነዘረባቸው ገለጹ

የኮሎምቢያው ፕሬዝዳንት ጉስታቮ ፔትሮ በህይወታቸው ላይ ያነጣጠረ የግድያ ሙከራ እንደተፈጸመባቸውና ሙከራውንም በሰላም ማለፋቸውን በይፋ አስታወቁ።

ፕሬዝዳንቱ በሰጡት መግለጫ፣ ጥቃቱ የተሰነዘረው ከልጃቸው ጋር በሄሊኮፕተር በመጓዝ ላይ በነበሩበት ወቅት መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ፣ ለወራት ያህል በሀገሪቱ በረቀቀ ሁኔታ በሚንቀሳቀሱ የእፅ አዘዋዋሪ ቡድኖች ኢላማ ተደርገው ቆይተዋል።

የኮሎምቢያ የደህንነት ምንጮችን ዋቢ አድርገው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ከጥቃቱ ጀርባ “የባህረ ሰላጤው ጎሳ” (Gulf Clan) በመባል የሚታወቁትና በሀገሪቱ ትልቁን የእፅ ዝውውር የሚቆጣጠሩት ቡድኖች ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ተጠርጥሯል።

ፕሬዝዳንት ፔትሮ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በሀገሪቱ “ሁለንተናዊ ሰላም” (Total Peace) ለማምጣት የጀመሩት ጥረትና በእፅ አዘዋዋሪዎች ላይ የወሰዱት ጠንካራ እርምጃ ለጥቃቱ መነሻ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም፣ ጥቃቱ የተፈጸመው በሄሊኮፕተር በሚጓዙበት ወቅት ቢሆንም፣ በደህንነት አባላት ጥንቃቄና በበረራ ባለሙያዎች ብቃት ምክንያት ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስ ማምለጥ መቻላቸውን ገልጸዋል።

ይህ ሙከራ በኮሎምቢያ ፖለቲካዊ መረጋጋት ላይ ከፍተኛ ስጋት የፈጠረ ሲሆን፣ የተለያዩ የዓለም ሀገራት መሪዎች ድርጊቱን እያወገዙ ይገኛሉ።

የኮሎምቢያ ፖሊስና የደህንነት ተቋማት በጉዳዩ ላይ ሰፊ ምርመራ እያደረጉ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ በፕሬዝዳንቱና በቤተሰቦቻቸው ላይ የሚደረገው ጥበቃም በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጠናከር ተደርጓል።

የግራ ዘመም ፖለቲከኛ የሆኑት ጉስታቮ ፔትሮ፣ በኮሎምቢያ ለበርካታ አስርት ዓመታት የዘለቀውን የእርስ በርስ ግጭት ለማስቆም ከታጠቁ ቡድኖች ጋር የሰላም ንግግር እያደረጉ መሆኑ ይታወቃል።

ሆኖም ይህ የሰላም ጥረት በከፍተኛ ወንጀልና በእፅ ዝውውር ከሚተዳደሩ አካላት ከፍተኛ ተቃውሞና ዛቻ እየደረሰበት ይገኛል ሲል የዘገበው አልጀዚራ ።

ልኡል ወልዴ

የካቲት 04/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *