በሱዳን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በትምህርት ቤት ላይ ባደረሰዉ የድሮን ጥቃት ሁለት ህጻናት መገደላቸዉ ተገለጸ

በደቡብ ኮርዶፋን ግዛት በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ላይ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አድርሶታል በተባለ የድሮን ጥቃት ሁለት ህጻናት ሲገደሉ፤ ሌሎች 12 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል፡፡

የኮርዶፋን ግዛት ከሚያዝያ 2023 ጀምሮ በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሹ መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት እጅግ አስከፊ ውጊያ የሚታይበት ስፍራ ሆኗል።

ኤል-ራሃድ የሰሜን ኮርዶፋን ግዛት ዋና ከተማ የሆነችውን ኤል-ኦቤድን ከነጭ አባይ ወንዝ ጋር የሚያገናኝ ቁልፍ መስመር ላይ ትገኛለች፤ ይህም መስመር የጦር ሠራዊቱ ወደ ዋና ከተማዋ ካርቱም የሚደርስበት ዋነኛው መስመር ነው።

ከተማዋ ባለፈው የካቲት ወር በኤል-ኦቤድ ላይ ተጥሎ የነበረውን የረጅም ጊዜ ከበባ ለመስበር ጦር ሠራዊቱ ወደ ምዕራብ ባደረገው ፈጣን ጥቃት አማካኝነት በድጋሚ በሠራዊቱ ቁጥጥር ሥር ውላለች።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ሰፊውን የምዕራብ ዳርፉር ክልል ከቀሪው የአገሪቱ ክፍል ጋር የሚያገናኘውን የምስራቃዊ አውራ ጎዳና ላይ ተከታታይ የድሮን ጥቃቶችን በመሰንዘር ኤል-ኦቤድን በድጋሚ ለመክበብ እየሞከረ ይገኛል።

ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለህልፈት የዳረገ ሲሆን፤ ወደ 11 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎችን ደግሞ በማፈናቀል በዓለም ላይ ትልቁን የረሃብ እና የመፈናቀል ቀውስ ፈጥሯል።

በተጨማሪም ጦርነቱ አገሪቱን ለሁለት የከፈለ ሲሆን፤ ሠራዊቱ ሰሜኑን፣ መካከለኛውን እና ምስራቁን ክፍል ሲቆጣጠር፤ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እና አጋሮቹ ደግሞ ምዕራቡን እና የተወሰኑ የደቡብ ክፍሎችን ተቆጣጥረዋል።

በሁለት ሳምንታት ውስጥ ብቻ በደረሱ የድሮን ጥቃቶች ወደ 90 የሚጠጉ ንጹሐን ዜጎች ሲገደሉ፤ 1መቶ42 ደግሞ መቁሰላቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ በዚህ ሳምንት መግለጻቸዉን አስታዉሶ አፍሪካ ኒዉስ ነዉ የዘገበዉ፡፡

እስከዳር ግርማ

የካቲት 05/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *