የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ውስጥ ለኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ግንባታ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን 80 በመቶ ያህሉን ከሀገር ውስጥ አቅራቢዎች ማግኘቱን ገለጸ።
ተቋሙ የሀገር ውስጥ አምራቾችን በማበረታታት 3 ሺህ 9 መቶ 44 የዲስትሪቢውሽን ትራንስፎርመሮች፤ከ32 ሺህ ሜትር በላይ ኬብልና ኮንዳክተሮች፤ 97 ሺህ የትራንስፎርመር ፕሮቴክሽን ዕቃዎች እንዲሁም 32 ሺህ ኢንሱሌተሮች እና ከ201 ሺህ በላይ የተለያዩ የሀርድዌር ዕቃዎችን በሀገር ውስጥ አቅርቦት መሸፈን መቻሉን አሳውቁዋል።
አገልግሎቱ የአቅርቦት ውስንነትን ለመቅረፍና የደንበኞችን ጥያቄ በፍጥነት ለመመለስ አዳዲስ አሰራሮችን በመከተል ላይ እንደሚገኝ ያሳወቀ ሲሆን አምራቾች ጥራቱን የጠበቀ ምርት እንዲያቀርቡ ተከታታይ የቴክኒክ እገዛ እየተደረገላቸው እንደሚገኝም ገልፁዋል።
በተጨማሪም በውል ስምምነት መሰረት የምርቶቹ ጥራት እየተረጋገጠ ለስራ እንዲውሉ ይደረጋል ሲል አገልግሎቱ አሳውቁዋል፤ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ መተካት የውጭ ምንዛሬን ከመታደጉ ባለፈ የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን ያነቃቃልም ብሉዋል፡፡
የግብዓት አቅርቦት እጥረት ለደንበኞች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት አንዱ ማነቆ ነበር ያለው አገልግሎቱ ፤ አሁን ግን ሀገር በቀል አምራቾችን በማበረታታትና ያልተሟሉትን ከውጭ በማስገባት ችግሩን ለመፍታት በትኩረት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል ፡፡
ይህ እርምጃ መንግስት የጀመረውን ሀገር በቀል ኢኮኖሚ የማጠናከር ስትራቴጂ ተግባራዊ ለማድረግ የተወሰደ ትልቅ ስኬት ተደርጎ ተወስዷ።
የካቲት 05/2018 ዓ.ም
