አሰልጣኝ ቶማስ ቱኸል በእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ለተጨማሪ ዓመታት የሚያቆያቸውን አዲስ ኮንትራት ፈርመዋል። በአዲሱ ውላቸው መሰረትም ጀርመናዊው እስከ ዩሮ 2028 ድረስ የሶስቱ አናብስት አለቃ ሆነው ይቆያሉ ማለት ነው።
ቱኸል የቡድኑን ሀላፊነት የተረከቡት በጥር 2025 ሲሆን ቀደም ሲል የነበረው ስምምነት በመጪው ክረምት ከሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ በኋላ የሚያበቃ ነበር።
አሰልጣኙ ስለ ውሳኔያቸው ሲናገሩ “እስካሁን ከእንግሊዝ ብ/ቡድን ጋር ባሳለፍኳቸው እያንዳንዱ ደቂቃዎች ደስተኛ ነኝ። አዲስ የኮንትራት ውል ሲቀርብልኝ ምንም ያላንገራገርኩትም ለዚህ ነው። ይሄንን በማድረጌም ኩራት ይሰማኛል” ብለዋል።
የእንግሊዝ እግር ኳስ ማህበር በበኩሉ፥ ወደ ዓለም ዋንጫው ከመግባቱ በፊት ቀጣይነትን ለማረጋገጥ እና በአሰልጣኙ የወደፊት ቆይታ ላይ የሚነሱ ግምቶችን ለማስቀረት ይህንን ውሳኔ ማሳለፉን ገልጿል።
ምስጋናው ታደሰ
የካቲት 5/2018 ዓ.ም
