አካል ጉዳተኛ ዕጩ ተወዳዳሪዎች እና ፈተናዎቻቸው

አካል ጉዳተኛ ዕጩ ተወዳዳሪዎቻችን እንግልት እየደረሰባቸው ነው ሲል የዎላይታ ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ አሳወቀ

የንቅናቄው አካል ጉዳተኛ የሆኑ የስራ አስፈጻሚ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ፊርማ ለማሰባሰብ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ለእስራት ተዳርገው እንደነበርም ገልጿል፡፡

የዎላይታ ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ የብሔራዊ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ታዲዮስ ጭለሾ ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር በነበራቸው ቆይታ በምርጫ አካታችነትን በተመለከተ በፌደራል ደረጃ ስራዎች ቢታዩም በክልል፣ በዞን እና በወረዳ ደረጃ በርካታ ክፍተቶች እንደሚታዩና የገዢው ፓርቲ ሰዎችም ተጽዕኖ እያደረጉባቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ፓርቲያቸው ሃገርዓቀፍ መሆኑን የተናገሩት አቶ ታዲዮስ በተለያዩ ቦታዎች ያሉ ችግሮችን መመልከት እንደቻሉና በተለይ የጸጥታ ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች ላይ ከአካል ጉዳተኞች በተጨማሪ ሴቶችም ሆኑ ወጣቶች ለመሳተፍ እንደሚቸገሩ አንስተዋል፡፡

”እኛ አካባቢ ዘግይቶ ጥር 18 በተጀመረው የዕጩ ምዝገባ በዊልቸር ላይ ሆነው ለመመዝገብ የሄዱ አካል ጉዳተኞችንም ሆነ ረዳት ይዘው የሄዱ አይነስውራንን  ‘ለአካል ጉዳተኝነታችሁ ማረጋገጫ አምጡ‘ ስለሚሏቸው ለመመላለስ ይገደዳሉ” ብለዋል፡፡

”ለማረጋገጫ የአካል ጉዳተኞች ማህበር የሰጣቸው መታወቂያ አለ፤ ነገር ግን መታወቂያውን አይሆንም አሉ፡፡ ቀበሌ ሄደው ደብዳቤ ለማጻፍ በሚሞክሩበት ጊዜ በትንሹ ከአንድ ሺ ብር ጀምሮ ይከፍላሉ፤ ምክንያቱም ተፎካካሪ ፓርቲዎችን የሚመለከቱት እንደጠላት ነው” ሲሉም የንቅናቄው የብሔራዊ ጽ/ቤት ሃላፊው አክለዋል፡፡

”የዎላይታ ልማት ማህበር (ዎልማ)፣ የቀይ መስቀል እና የጤና መድህን ድጋፍ ሁሉ ይጠየቃሉ፡፡ ይህ ሁሉ ፈተና ሲደራረብባቸው ፓርቲያችን ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ጽፏል” በማለት ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡

”ከአስራ አምስቱ የዎላይታ ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ አባላት መካከል የሆኑ ንግስት ሚልኪያስ እና ጃምቦ ጃፋሮ የተባሉ አካል ጉዳተኛ የስራ አስፈጻሚዎች፣ የዕጩ ተወዳዳሪነት ፊርማ ዞረው እያስፈረሙ በነበረበት ወቅት ለእስር ተዳርገው ነበር” ያሉ ሲሆን፣ ድርጊቱ የተፈጸመውም በዎላይታ ሶዶ ከተማ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

አካል ጉዳተኛ የስራ አስፈጻሚ አባላቱን ከእስር ለማስፈታት የብሔራዊ ጽ/ቤት ሃላፊው ከጎፋ ዞን ለመምጣት መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የአካባቢው አመራሮች ”አንዲት የፓርቲያችን አባል የሆነች አካል ጉዳተኛ እና የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ የነበረች ሴት ሞጋች ጥያቄዎችን የምታነሳ በመሆኗ ምክንያት ‘ለእሷ ደብዳቤ ጽፋችሁ ሌላ ቀይሩ‘ እስከማለት ደርሰዋል” ሲሉ አቶ ታዲዮስ ጭለሾ ገልጸዋል፡፡

ይህም አካል ጉዳተኛዋን አባል የስነ ልቦና ጫና እንደፈጠረባት ነው የንቅናቄው የብሔራዊ ጽ/ቤት ሃላፊው የገለጹት፡፡

በንቅናቄው ውስጥ ካሉ አካል ጉዳተኞች መካከል 120 ያህሉ መስማት የተሳናቸው መሆናቸውንና የምርጫውን እንቅስቃሴ በተመለከተ በምልክት ቋንቋ እንዳልተዘጋጀላቸውም ጠቅሰው፣ ለእነዚህ አባሎቻቸው ምርጫ ቦርድ በምልክት ቋንቋ እንዲያዘጋጅላቸው ሁለት ጊዜያት ያህል በደብዳቤ መጠየቃቸውን ነግረውናል፡፡

ምርጫ ቦርድም ጥረት እያደረገ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

አዲስአለም አበበ

የካቲት 06/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *