ሺ አለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ስራ ሳይንቅ በሚሰራበት ወቅትም ሆነ ብክነትን ለማስቀረት በሚያደርገው ጥረት ”እንዴት እዚህ ትገኛለህ” የሚል አስተያየት እንደሚሰጠው ገልጿል፡፡
ሺ አለቃ ኃይሌ ይህን የገለጸው በ‘ሪች ፎር ቼንጅ‘ ድጋፍ የተደረገላቸው የማህበረሰብ ስራ ፈጣሪዎች የካቲትበ 6፣ 2018 ዓ.ም ስራዎቻቸውን በኃይሌ ግራንድ ሆቴል ለዕይታ ባቀረቡበት መርሐ ግብር ባደረገው ንግግር ነው፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ በሪች ፎር ቼንጅ ኢትዮጵያ ድጋፍ እየተደረገላቸው የሚገኙ በሃሳብ ደረጃ እና በማደግ ላይ ያሉ የማህበረሰብ ስራ ፈጣሪዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ የተወሰኑት ችግር ፈቺ የንግድ ስራ ፈጠራዎቻቸውን ለዕይታ አቅርበዋል፡፡ ለዕይታ የቀረቡት ፈጠራዎች ከተረፈ ምርት ወይም ቆሻሻ ተብለው ከተጣሉ ግብዓቶች የተሰሩ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ከሌሎች እንግዶች ጋር በመሆን ለዕይታ የቀረቡትን ስራዎች የጎበኘው ሺ አለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ለስራ ፈጣሪዎቹ ያለውን አድናቆት በመግለጽ የማበረታቻ ንግግር አድርጓል፡፡ ኃይሌ ስራ ሳይንቅ በሚሰራበት ወቅትም ሆነ ብክነትን ለማስቀረት በሚያደርገው ጥረት ‘እንዴት እዚህ ትገኛለህ‘ የሚል አስተያየት እንደሚሰጠው በመጥቀስ እንዲህ ያሉ አስተሳሰቦች ተገቢ እንዳልሆኑ ጠቁሟል፡፡
” እኔ ከሚገጥሙኝ ከባድ ችግሮች መካከል፣ የሆነ ስራ ስሰራ ሲያዩ ‘…ኧረ በናትህ ይቅር ይበልህ፣ እንዴት እዚህ ጋር ትገኛለህ‘ ይሉኛል” ያለው ሺ አለቃ ኃይሌ ”እኔን የሚጥለኝ የተመረተው ሳይሆን ለማምረት የሚወጣውና የተጣለው ነው፤ ድርጅትን የሚጥለው ይህ ነው” ሲል ተናግሯል፡፡
ኢትዮጵያውያን የምንተፋፈረው ጉረኞች ስለሆንን ነው ያለ ሲሆን፣ የተጣሉ ግብዓቶችን በመጠቀም ፈጠራዎቻቸውን ያቀረቡ የማህበረሰብ ስራ ፈጣሪዎች በአንድ ጊዜ ሁለት ተግባር ማከናወናቸውን በማንሳት አድናቆቱን ገልጿል፡፡
የስራ ፈጣሪዎቹ የአካባቢ ብክለትን ከመከላከል ባሻገር ወደ ንግድ ስራ መቀየራቸውን በማበረታታት በዚህ ረገድ የሆቴሎቹን ተሞክሮ እና ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች አጋርቷል፡፡
ሺ አለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ለማህበረሰብ ስራ ፈጣሪዎቹ የስልጠና እና የገንዘብ ድጋፍ ያደረገውን ሪች ፎር ቼንጅ ኢትዮጵያን አመስግኗል፡፡
አዲስአለም አበበ
የካቲት 09/2018 ዓ.ም
