የአፍሪካ ኅብረት ባርነትንና ቅኝ ግዛትን በሰው ልጅ ላይ እንደተፈጸሙ ወንጀሎች የሚገልጽ የውሳኔ ሐሳብ አጸደቀ

በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት በተካሄደው ጉባኤ ላይ የተሳተፉት የአፍሪካ ኅብረት መሪዎች፤ ባርነትን፣ ከቀዬ ማፈናቀልን እና ቅኝ ግዛትን እንደ ዘር ማጥፋት እና በአፍሪካ ሕዝቦች ላይ እንደተፈጸሙ ወንጀሎች የሚገልጽ የውሳኔ ሐሳብ አጽድቀዋል።

ሊቀመንበሩ ማህሙድ አሊ ዩሱፍ፤ ጉባኤው ቅኝ ግዛትን በሰው ልጅ ላይ እንደተፈጸመ ወንጀል ዕውቅና ይሰጣል። ይህ በጣም አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም ጉባኤው ለፍልስጤም እና ለፍልስጤም ሕዝብ ያለውን አጋርነት ይገልጻል ብለዋል።

አባል ሀገራቱ ኅዳር 21 ቀን ‹‹ለአፍሪካ ሰማዕታት እና ለአትላንቲክ የባርያ ንግድ፣ ለቅኝ ግዛት እና ለአፓርታይድ ሰለባዎች መታሰቢያ ቀን›› ሆኖ እንዲከበር ተስማምተዋል።

መሪዎቹ ጉዳዩን ክትትል እያደረጉበት እንደሚቆዩና የውሳኔ ሐሳቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና እንዲያገኝ በጋራ እንደሚሠሩም ገልጸዋል።

የጋናዉ ፕሬዝዳንት ጆን ማሃማ፤ የአፍሪካ ኅብረት አባል ሀገራት በአትላንቲክ ባሪያ ንግድ ሳቢያ የደረሱ ታሪካዊ በደሎችን ዕውቅና ለመስጠት የታለመውን ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ እንደገለጹት፤ ይህ እርምጃ ያለፈውን ታሪክ ባይሰርዘውም፣ አፍሪካውያንን ለባርነት መገበያየትና ዘርን መሰረት ያደረገ ባርነት ዘመናዊውን ዓለም በመቅረጽ ረገድ ትልቅ ሚና የነበራቸው ከባድ ወንጀሎች መሆናቸውን በይፋ ዕውቅና ይሰጣል ብለዋል።

ታሪካዊ እውነቶችን መጋፈጥ የ‹‹ሞራል ጀግንነት›› እንጂ የመከፋፈል ጉዳይ አለመሆኑን ያመለከቱት ማሃማ፤ የባርነት ተጽዕኖዎች ዛሬም በመዋቅራዊ እኩልነት እጥረት፣ በዘር መድልዎ እና በኢኮኖሚ አለመመጣጠን መልክ መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

የውሳኔ ሐሳቡ መጽደቅ መጨረሻው አይሆንም ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ከጸደቀ በኋላ ጋና ከተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ፣ ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን፣ ከሚመለከታቸው የተመድ አካላት እና ፍላጎት ካላቸው አባል ሀገራት ጋር ግንኙነቷን ትቀጥላለች ብለዋል።

ሀና ሰይፉ

የካቲት 09/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *