አንጎል ከሞት በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ስራውን እንደሚቀጥል የሚያሳይ አዲስ የህክምና ጥናት ይፋ ሆነ፡፡

በኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ በላንጎን የህክምና ማዕከል የተካሄደ አዲስ ጥናት፣ የሰው ልጅ ልብ መምታቱን ካቆመ በኋላም አንጎል ለተወሰነ ጊዜ ንቁ ሆኖ ሊቆይ እንደሚችል አረጋግጧል።

በዶክተር ሳም ፓርኒያ የተመራው ይህ ምርምር እንደሚያሳየው፣ በህክምና ትርጓሜ “ሞተዋል” ተብለው የታወጀባቸው ሰዎች ልባቸው ከቆመ በኋላም በክፍሉ ውስጥ የሚከናወኑ ድርጊቶችንና የዶክተሮችን ንግግር የመስማት እንዲሁም የማስተዋል ከፍተኛ ዕድል አላቸው ተብሏል፡፡

ተመራማሪዎቹ በ25 ሆስፒታሎች ውስጥ በልብ ድካም ምክንያት ህይወታቸው አልፎ በህክምና ጥረት የተመለሱ ታካሚዎችን የመረመሩ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 40 በመቶ የሚሆኑት በወቅቱ ሙሉ ንቃተ-ህሊና እንደነበራቸውና ከሰውነታቸው ተለይተው በክፍሉ ውስጥ የሚሆነውን ነገር ሁሉ በትክክል ይመለከቱ እንደነበር ገልጸዋል።

በጥናቱ ወቅት በተደረገ የአንጎል የኤሌክትሪክ ምርመራ (EEG)፣ ልብ ከቆመ ከ35 እስከ 60 ደቂቃዎች ባለው ጊዜ ውስጥ ከአስተሳሰብና ከትውስታ ጋር የተያያዙ የአንጎል ሞገዶች በከፍተኛ ሁኔታ ሲንቀሳቀሱ ተስተውለዋል።

ይህ በሞት አፋፍ ላይ የሚከሰት የአንጎል የሀይል መርጨት፣ ግለሰቦች ያለፈ ህይወታቸውን እንደ ፊልም በአይነ ህሊናቸው እንዲመለከቱ እንደሚያደርጋቸውም ተመራማሪዎቹ አብራርተዋል።

ይህም ቀደም ሲል አንጎል ልብ ከቆመ ከ10 ደቂቃ በኋላ ስራ ያቆማል ተብሎ ይታመን የነበረውን ሳይንሳዊ ግምት የሚቀይር ሲሆን፣ ወደፊት የልብ ድካም ለደረሰባቸው ሰዎች የሚሰጠውን የህክምና እርዳታ ለማሻሻል ትልቅ መንገድ ይከፍታል መባሉን ኒው ዮርክ ፖስት ዘግቧል፡፡

ሐመረ ፍሬው

የካቲት 11/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *