የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጣይፕ ኤርዶዋን እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችውን እውቅና ያወገዙ ሲሆን፤ድርጊቱ ሕገወጥና ለአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት ስጋት መሆኑን ገልጸዋል።
የክልሉ አገራት ችግሮቻቸውን ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት እንዲፈቱ ያሳሰቡት ፕሬዝዳንቱ፤ ቱርክ ለሶማሊያ ሉዓላዊነት ያላትን ድጋፍም አረጋግጠዋል።
ሶማሊያ በበኩሏ ለውሳኔው ድጋፍ ሰጥታለች ስትል ከከሰሰቻት የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ጋር ያላትን ግንኙነት ያቋረጠች ሲሆን፤ ከኳታር እና ከቱርክ ጋር ያላትን ወታደራዊ ትብብር አጠናክራለች።
ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን እስራኤል ተገንጣይዋን የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ እውቅና ለመስጠት የወሰደችውን እርምጃ ተችተዉ፤ ውሳኔው ለሶማሊላንድም ሆነ ለአካባቢው አገራት ምንም ዓይነት ጥቅም እንደማይሰጥም ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ታኅሳስ ወር ድርጊቱን ሕገ-ወጥና ተቀባይነት የሌለው በማለት ማውገዛቸውን ያስታወሱ ሲሆን፤ እስራኤል የአፍሪካ ቀንድን ለማተራመስ እየሞከረች ነው ሲሉ ከሰዋል።
ኤርዶዋን፤የክልሉ ችግሮች መፈታት ያለባቸው በክልሉ አገራት በራሳቸው እንደሆነ እናምናለን፤ የአፍሪካ ቀንድም ለባዕድ ኃይሎች የትግል አውድማ መሆን የለበትም ብለዋል።
ከዚህ አንጻር እስራኤል ለሶማሊላንድ እውቅና መስጠቷ ሶማሊላንድንም ሆነ የአፍሪካ ቀንድን እንደማይጠቅም በድጋሚ ላረጋግጥ እወዳለሁ ብለዋል።
ትናንት በአዲስ አበባ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንቱ፤ ቱርክ ለክልሉ አገራት ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ትልቅ ዋጋ እንደምትሰጥና አዲስ ግጭት እንደማትፈልግ ገልጸዋል።
ቱርክ የሶማሊያን የደህንነት ኃይሎች በማሰልጠን እንዲሁም ከኢትዮጵያና ሌሎች አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በማጠናከር በአፍሪካ ያላትን ተጽዕኖ እያሰፋች ትገኛለች።
የሶማሊላንድን ጉዳይ ተከትሎ ሶማሊያ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የእስራኤልን ውሳኔ ደግፋለች በሚል ግንኙነቷን አቋርጣለች።
ሞቃዲሾ ከዚያ በኋላ ከኳታር ጋር የመከላከያ ስምምነት የተፈራረመች ሲሆን፤ቱርክ ደግሞ ለሶማሊያ መንግሥት ያላትን ድጋፍ ለማሳየት በሶማሊያ ለሚገኘው የጦር ሰፈሯ የጦር ጄቶችን ልካለች ያለዉ አፍሪካ ኒዉስ ኢንግሊሽ ነዉ።
እስከዳር ግርማ
የካቲት 11/2018 ዓ.ም
