ኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ ስዊዘርላንድ ከሚገኙ አጋሮቹ በተገኘ ከ2.8 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ፣ አዳዲስ የቤተሰብና የማህበረሰብ ማጠናከሪያ ፕሮጀክቶችን ማስጀመሩን ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
ድርጅቱ በዚህ ከፍተኛ በጀት ሦስት አዳዲስ ፕሮጀክቶችን የሚጀምር ሲሆን፣ ቀደም ሲል ሲያካሂዳቸው የነበሩ ሌሎች ሦስት ፕሮጀክቶችንም አጠናክሮ ለማስቀጠል መወሰኑ ተገልጿል፡፡
የኤስ ኦ ኤስ የህጻናት መንደሮች በኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ዳይሬክተር አቶ ሣህለማርያም አበበ እንደገለጹት፣ አዲሶቹ ፕሮጀክቶች በሲዳማ ክልል (አለታወንዶ ና ይርጋለም) እና በኦሮሚያ ክልል (ያቤሎ) የሚተገበሩ ሲሆን፤ በአዋሳ፣ ሻሸመኔና ላሊበላ ያሉ ፕሮጀክቶች ደግሞ ከ2026 ጀምሮ በዚሁ በጀት ተጠናክረው ይቀጥላሉ
የፕሮጀክቶቹ ዋነኛ ዓላማ ህፃናትና ወጣቶች ከቤተሰብ መፍረስ ስጋት ነፃ ሆነው በቤተሰባዊ እንክብካቤ እንዲያድጉ ምቹ ሁኔታ መፍጠር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በሚቀጥሉት ሦስት እና አራት ዓመታት ውስጥ ወደ 420 ሺህ የሚጠጉ ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ እንደታቀደ እና ይህንንም ግብ ለማሳካት የገቢ ምንጭ ዕድሎችን መፍጠር፣ የቁጠባና ብድር ማህበራትን እንዲሁም የህፃናት ጥበቃ ሥርዓቶችን ማጠናከር ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል፡፡
ድርጅቱ ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ በገለልተኝነት ሲሰራ የቆየ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም በቀላፎና በሆሳእና ተጨማሪ የ251 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክቶችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ሐመረ ፍሬው
የካቲት 12/2018 ዓ.ም
