በናይጄሪያ ሕገ-ወጥ የማዕድን ቁፋሮ ሰፊ ችግር ሲሆን፣ ተግባራቱም የመንግሥት ቁጥጥር እና የደህንነት ጥበቃ ፕሮቶኮሎች የጎደሏቸው ናቸው።
በመካከለኛው ናይጄሪያ በሚገኝ የአንድ ማዕድን ማውጫ ቦታ ቢያንስ 37 የማዕድን ቆፋሮዎች በካርቦን ሞኖክሳይድ ጋዝ መመረዝ ምክንያት ህይወታቸው ማለፉን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ረቡዕ ጠዋት በፕላቶ ግዛት ዋሴ አካባቢ በሚገኘው ካምፓኒ በተባለ ማህበረሰብ ውስጥ የተከሰተው ይህ አሰቃቂ አደጋ፣ 25 ሰዎች ሆስፒታል እንዲገቡ ማድረጉን ሮይተርስ የፖሊስ ምንጮችን እና ያገኘውን የጸጥታ ሪፖርት በመጥቀስ ገልጿል።
የመንግሥት ባለሥልጣናት እንደገለጹት፣ አደጋው የደረሰው ተዘግቶ በቆየ የሊድ (Lead) ማዕድን ማውጫ ውስጥ ተከማችተው የነበሩ ማዕድናት ገዳይ የሆኑ ጋዞችን በመልቀቃቸው ነው።
መንግሥት ትክክለኛውን ቁጥር ባይገልጽም “በርካቶች ሳይሞቱ አይቀሩም” ብሏል።
ናይጄሪያ የጠንካራ ማዕድናት ሚኒስትር ዴሌ አላኬ እንደተናገሩት፣ አደጋው የደረሰው የአካባቢው ነዋሪዎች የጋዙን መርዛማነት ሳያውቁ ማዕድን ለማውጣት ወደ ዋሻው ውስጥ በገቡበት ወቅት ጋዙን በማተንፈሳቸው ነው።
በአሁን ወቅት የጸጥታ ኃይሎች ተጨማሪ ሰዎች ወደ ቦታው እንዳይገቡ አካባቢውን ዘግተውታል። የፌደራል መንግሥቱም አጠቃላይ ምርመራ እስኪደረግ ድረስ በአደጋው አካባቢ የሚካሄዱ ማናቸውም የማዕድን ቁፋሮዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ አዟል።
ፕላቶ ግዛት በታሪክ በማዕድን ቁፋሮ የምትታወቅ ሲሆን፣ ዋና ከተማዋ ጆስ “የቆርቆሮ ከተማ” በመባል ትታወቃለች፤ ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የማዕድን እንቅስቃሴዎች ቀንሰዋል።
በናይጄሪያ መሰል አደጋዎች ከዚህ ቀደምም የተከሰቱ ሲሆን ባለፈው ዓመትም በዛምፋራ ግዛት በከባድ ዝናብ ወቅት ድንጋይ በሕገ-ወጥ ማዕድን አውጪዎች ላይ በመናዱ 18 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።
ሀና ሰይፉ
የካቲት 12/2018 ዓ.ም
