የፖለቲካ ፓርቲዎች አካል ጉዳተኞችን በገቢ ምንጭነት እንዳይጠቀሙባቸው ተጠየቀ

የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጠውን የመንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ብቻ አካል ጉዳተኛ ያልሆኑ ሰዎችን እንደ አካል ጉዳተኛ አድርገው የመመዝገብና እውነተኛ ውክልና የመንፈግ ዝንባሌ እንዳይታይባቸው የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ አካል ጉዳተኞች ማኅበር ጠይቋል።

የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ አካል ጉዳተኞች ማኅበር ዋና ዳይሬክተር አቶ አሙሴ ጥላሁን ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ፓርቲዎች አካል ጉዳተኞችን በቁርጠኝነት በማሳተፍ ረገድ ትልቅ ክፍተት አለባቸው ብለዋል።

ማኅበሩ በቅርቡ ባደረገው ጥናት፣ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች አካል ጉዳተኞችን በውሳኔ ሰጪነት ቦታዎች ላይ ከማሳተፍ ይልቅ ለታይታና ለገቢ ምንጭነት እንደሚጠቀሙባቸው ገልጿል።

ዳይሬክተሩ አያይዘውም በጎረቤት ሀገራት እንደ ኬንያና ኡጋንዳ ያሉ ልምዶችን በመጥቀስ፣ በኢትዮጵያም አካል ጉዳተኞች በሕግ የተደገፈ ቋሚ የፓርላማ መቀመጫና እውነተኛ ውክልና ሊኖራቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።

አቶ አሙሴ ጥላሁን እንደገለጹት፣ በስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ 99 የሚደርሱ አካል ጉዳተኞች በፓርቲዎች እጩ ሆነው ቢቀርቡም፣ ወደ ፓርላማ መግባት የቻሉት ግን ሦስት ብቻ ናቸው። ይህም ፓርቲዎቹ ለእጩዎቻቸው በቂ የምርጫ ቅስቀሳና ድጋፍ አለማድረጋቸውን ያሳያል ብለዋል።
ይባስ ብሎም ከዚህ ቀደም አንዳንድ ፓርቲዎች የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ አካል ጉዳተኛ ያልሆኑ ሰዎችንና የመንገድ ላይ ተመጽዋቾችን ሳይቀር “የእኛ አባልና አካል ጉዳተኛ ናቸው” በማለት እስከመመዝገብ መድረሳቸውንና ጉዳዩም በፍርድ ቤት የተያዘ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ አካል ጉዳተኞች ማኅበር ፓርቲዎች ከአመለካከት ችግር ወጥተው አካል ጉዳተኞችን በቁርጠኝነት እንዲያሳትፉም ጥሪ አቅርበዋል።

አዲስአለም አበበ

የካቲት 13/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *