‹‹የመሬት የልብ ትርታ›› በመባል የሚታወቀው የሹማን ሬዞናንስ (Schumann Resonance) የንዝረት መጠን በየካቲት ወር ባልተለመደ ሁኔታ መጨመሩን የጠፈር አየር ሁኔታ ተቆጣጣሪዎች አስታዉቀዋል።
ይህ ተፈጥሯዊ የኤሌክትሮማግኔቲክ ሞገድ አብዛኛውን ጊዜ በሰከንድ 7.83 ጊዜ የሚርገበገብ ቢሆንም፤ በፀሐይ ላይ በተከሰተ የጨረር ፍንዳታ ምክንያት መዛባት እንደታየበት ተገልጿል።
የመሬት ንዝረት መዛባት ከሰዎች የአዕምሮ ሞገድ ጋር ተመሳሳይ ድግግሞሽ ስላለው፤ እንደ ራስ ምታት፣ ማዞር፣ የእንቅልፍ መዛባት እና በጆሮ ውስጥ የሚሰማ የማያቋርጥ ጩኸት ያሉ የጤና እክሎችን ሊያስከትል እንደሚችል ተጠቁሟል።
በተለይም አዕምሮ በእረፍት ወቅት የሚያመነጨው ሞገድ ከመሬት ተፈጥሯዊ ድምፅ ጋር የተሳሰረ በመሆኑ፤ድንገተኛ የንዝረት ለውጥ የሰውን ልጅ የእንቅልፍ ዑደት ሊያናጋ ይችላል የሚል ስጋት መኖሩ ተነግሯል፡፡
ምንም እንኳን ባለፈው ወር የንዝረት መለኪያው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረ ቢሆንም፤ ሳይንቲስቶች ክስተቱ በሰው አካል ላይ ስለሚያደርሰው ቀጥተኛ ጉዳት ገና ተጨማሪ ጥናት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የጃፓን ተመራማሪዎችም የታዩት የጤና ምልክቶች ከሌሎች አካባቢያዊ ሁኔታዎች ጋር ሊያያዙ እንደሚችሉ በመጠቆም፤ ጉዳዩን በጥንቃቄ መከታተል እንደሚገባ አሳስበዋል ሲል ኒውዮርክ ፖስት ዘግቧል፡፡
ሐመረ ፍሬዉ
የካቲት 16/2018 ዓ.ም
