በእስራኤል እና በኢራን መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ በሀገር ውስጥ ያላቸውን የፖለቲካ ድጋፍ እያጠናከረላቸው ይገኛል።
ኔታንያሁ እንደ አያቶላ አሊ ካሜኒ ያሉ የኢራን መሪዎችን ኢላማ ያደረገ ጥቃት በመሰንዘር፣ ራሳቸውን እንደ “ታላቅ የጦርነት መሪ” እና እንደ ዘመኑ “ቸርችል” በማቅረብ ላይ ናቸው።
የቅርብ ጊዜ የሕዝብ አስተያየት ጥናቶች እንደሚያሳዩት 81 በመቶ የሚሆነው የእስራኤል ሕዝብ በኢራን ላይ የተሰነዘረውን ጥቃት ይደግፋል።
ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ እስራኤል በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለባትን ዲፕሎማሲያዊ ጫና እና ግንኙነት ሊያበላሽ እንደሚችል ስጋቶች አሉ።
የኢራን ጦርነት ኔታንያሁን በሀገር ውስጥ ሊረዳቸው ቢችልም እስራኤልን ግን በውጭው ዓለም ሊጎዳ ይችላል::
ባለፈው ሰኞ ብሪታንያ በሚታተመው “ቴሌግራፍ” (The Telegraph) ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ አርዕስት “ኔታንያሁ የዘመናችን ታላቅ የጦር መሪ ናቸው” ሲል አወድሷቸዋል።
ታዋቂው ወግ አጥባቂ ጋዜጠኛ ቻርለስ ሙር የጻፈው ይህ ጽሑፍ፣ ኔታንያሁን እንደ ዊንስተን ቸርችል በመመሰል፣ ለብዙ ዓመታት በኢራን ላይ ያተኮሩት ትኩረት እና ከሀማስ፣ ከሂዝቦላህ እንዲሁም ከቴህራን ጋር ያደረጉት ወታደራዊ ግጭት መካከለኛው ምስራቅን መልክ እያስያዘ መሆኑን ገልጿል።
የኢራኑን የበላይ መሪ አያቶላ አሊ ካሜኒን በመግደል የተጀመረው የወቅቱ የኢራን ጦርነት፣ በዚህ ዓመት መጨረሻ ምርጫ ለምትጠብቀው እስራኤል የኔታንያሁ ደጋፊዎችን በራስ መተማመን ጨምሯል።
የ”INSS” ጥናት እንደሚያሳየው 81% የእስራኤል ሕዝብ ጥቃቱን ሲደግፍ፣ 63% ደግሞ የኢራን አገዛዝ እስኪወድቅ ድረስ ዘመቻው እንዲቀጥል ይፈልጋሉ።
የተቃዋሚ መሪዎች ሳይቀሩ በወታደራዊ ዘመቻው ዙሪያ ከመንግስት ጎን ቆመዋል።
ኔታንያሁ ለብዙ አሥርተ ዓመታት ኢራንን የእስራኤል ዋነኛ የህልውና ስጋት አድርገው ሲገልጹ ቆይተዋል።
እስራኤል የ”ጥፋት ዘንግ” (Axis of Evil) የምትላቸውን የሀማስ፣ የሂዝቦላህ እና የኢራን መሪዎችን መግደሏን ተከትሎ፣ ኔታንያሁ ይህንን ወታደራዊ ስኬት በምርጫ ካርድ ለመቀየር “ኦፕሬሽን የሚያገሳ አንበሳ” (Operation Roaring Lion) በሚል ስያሜ ቅስቀሳ መጀመራቸው ተስተውሏል።
ሀና ሰይፉ
የካቲት 27/2018 ዓ.ም
