ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከሆነ፤አብዛኛው ወጪ በበጀት ያልተያዘ በመሆኑ የፔንታጎን መሥሪያ ቤት በቅርቡ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ መጠየቅ ይኖርበታል።
አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት በመጀመሪያዎቹ 100 ሰዓታት ውስጥ ብቻ ለዋሽንግተን 3.7 ቢሊየን ዶላር ወይም በቀን ወደ 9መቶ ሚሊየን ዶላር ገደማ ወጪ እንዳስከተለ ይገመታል።
ይህም በዋነኝነት ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሣሪያዎችና ጥይቶች ጥቅም ላይ በመዋላቸው የመጣ እንደሆነ አዲስ የተደረገ ጥናት አመልክቷል።
በዋሽንግተን የሚገኘው የስትራቴጂክ እና ዓለም አቀፍ ጥናቶች ማዕከል የተባለው የጥናት ተቋም ያደረገው ትንታኔ የጦርነቱን እጅግ ከፍተኛ ወጪ አጉልቶ አሳይቷል።
አሜሪካ በኢራን ላይ በረቀቁ የቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች እና ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ሥርዓቶች ጥቃት በፈጸመችበት በዚህ ወቅት ጦርነቱ ሰባተኛ ቀኑን ይዟል።
ተመራማሪዎቹ ማርክ ካንሲያን እና ክሪስ ፓርክ እንደገለጹት ከሆነ፤ በመጀመሪያዎቹ 100 ሰዓታት ውስጥ ከወጣው 3.7 ቢሊየን ዶላር ወይም በቀን 891.4 ሚሊየን ዶላር ውስጥ በበጀት አስቀድሞ የተያዘው ጥቂቱ ብቻ ሲሆን፤አብዛኛው ማለትም 3.5 ቢሊየን ዶላሩ በበጀት ያልተካተተ ነው።
ይህ ማለት ፔንታጎን በበጀት ያልተያዙ ወጪዎችን ለመሸፈን በቅርቡ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ መጠየቅ ይኖርበታል ማለት ሲሆን፤ ይህም ለትራምፕ አስተዳደር ፖለቲካዊ ፈተና እንደሚሆንና “ለጦርነቱ ተቃውሞ መነሻ” እንደሚሆን ተገልጿል።
የአገር ውስጥ የኑሮ ውድነት ስጋቶች፣ የዋጋ ግሽበት እና አሁን ደግሞ በጦርነቱ ምክንያት እየጨመረ የመጣው የነዳጅ ዋጋ በአሜሪካ ዜጎች ዘንድ ለጦርነቱ ያለውን ድጋፍ ሊቀንሰው ይችላል።
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ስለ ኦፕሬሽኖቹ ዝርዝር መረጃዎችን በውስን መልኩ ብቻ መስጠቱን የጠቀሱት ተመራማሪዎቹ፤ ትንታኔያቸው የተመሠረተው በኮንግረሱ የበጀት ጽሕፈት ቤት ግምቶች ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲሁም ለዋጋ ግሽበት እና ለተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ፍጥነት ሲባል 10 በመቶ ተጨማሪ ወጪ ታክሎበት እንደተሰላ ገልጸዋል።
በጥናቱ መሠረት አሜሪካ በመጀመሪያዎቹ 100 ሰዓታት ውስጥ ከ2 ሺህ በላይ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን የተጠቀመች ሲሆን፤ እነዚህን መሣሪያዎች መልሶ ለመተካት 3.1 ቢሊየን ዶላር እንደሚያስፈልግና ወጪውም በቀን በ758.1 ሚሊየን ዶላር እንደሚጨምር ተገምቷል።
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት፤ አሜሪካ በኢራን ላይ የምታደርገው ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር እንደሚችል ገልጸው፤ ይህም ተጨማሪ ተዋጊ አውሮፕላኖችን፣ የመከላከል አቅሞችን እና ተደጋጋሚ የቦምብ ጥቃቶችን እንደሚያካትት ተናግረዋል።
እስከዳር ግርማ
የካቲት 27/2018 ዓ.ም
