የማዳጋስካር ጊዜያዊ መሪ ሙሉ መንግሥቱን ሲበትኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ከሥራ አሰናብተዋል

የማዳጋስካር ፕሬዝዳንት ሚካኤል ራንድሪያኒሪና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሙሉ መንግሥቱን በትነዋል።

በመንግሥት ቃል አቀባይ በኩል በተሰጠ መግለጫ፤ መንግሥት ሥራውን ያቆመ ሲሆን ፕሬዝዳንት ራንድሪያኒሪና በአገሪቱ ሕገ-መንግሥት መሠረት ቀጣዩን ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሾሙ ተገልጿል።

ለመንግሥቱ መበተን እስካሁን የተሰጠ ግልጽ ምክንያት የለም።

ኮሎኔል ሚካኤል ራንድሪያኒሪና፣ የቀድሞው ፕሬዝዳንት በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ምክንያት በጥቅምት ወር ከአገር ከሸሹ ወዲህ የማዳጋስካር ጊዜያዊ መሪ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

በውኃ እና በኤሌክትሪክ እጥረት ምክንያት በወጣቶች መሪነት በመስከረም ወር የተጀመረው ተቃውሞ ወደ ትልቅ የሕዝብ እንቅስቃሴ የተቀየረ ሲሆን፤ መንግሥት እንቅስቃሴውን በኃይል ለማቆም ባደረገው ሙከራ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ማለፉና መቁሰላቸው ይታወሳል።

ባለፈው ዓመት፤የደቡብ አፍሪካ የልማት ማኅበር ወታደራዊ መሪዎቹ እስከ የካቲት መጨረሻ ምርጫ እንዲያካሂዱና ወደ ዲሞክራሲ የሚመለሱበትን የመንገድ ካርታ እንዲያሳውቁ አዝዞ ነበር።

ወደ ሥልጣን እንዲመጡ የረዳቸው የGen Z ንቅናቄን ጨምሮ፤ በመንግሥት ውስጥ አካታችነት እንዲኖር የሚጠይቅ ግፊት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ መጥቷል።

ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት፣ Gen Z እና Gen Y የተባሉ ሁለት የአክቲቪስት ንቅናቄዎች፣ በመንግሥት ደካማ አፈጻጸም እና በሕዝቡ ቅሬታ ምክንያት ራንድሪያኒሪና ከሥልጣን እንዲለቁ የ72 ሰዓት የጊዜ ገደብ ሰጥተዋል።

እነዚሁ ንቅናቄዎች በጥቅምት ወር የተሾሙትን አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሹመቱ ግልጽነት በጎደለውና በቂ ምክክር ባልተደረገበት ሁኔታ የተከናወነ ነው በሚል ውድቅ አድርገውት ነበር።

ሊዲያ ደሳለኝ

መጋቢት 01/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *