የእንጦጦ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ገዳም የ640 ሚሊዮን ብር የሕንፃ ግንባታውን ለማጠናቀቅ አገራዊ የድጋፍ ጥሪ አቀረበ

ጥንታዊውና ታሪካዊው የእንጦጦ ሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት አንድነት ገዳም፤ ለምዕመናን አገልግሎት የሚውልና በገንዘብ እጥረት የተቋረጠውን ባለ ስድስት ወለል ሁለገብ ሕንፃ ግንባታ ዳር ለማድረስ፣ የሦስት ቀናት ዓለም አቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ-ግብር ማዘጋጀቱን አስታወቀ።

ገዳሙ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ እንደሚሻ ገልጿል።

የእንጦጦ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ገዳም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ስር ከሚገኙ ጥንታውያንና ታዋቂ መንፈሳዊ ማዕከላት አንዱ ነው።

ገዳሙ በአሁኑ ወቅት ያለበትን የቦታ ጥበት ችግር ለመቅረፍና ለምዕመናን የሚሰጠውን አገልግሎት ለማዘመን ባለ ሁለት ቤዝመንት እና ባለ ስድስት ወለል ሁለገብ ሕንፃ ግንባታ ቢጀምርም፣ በፋይናንስ እጥረት ምክንያት ግንባታው ተገትቶ ይገኛል።

ገዳሙ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከተው፤ አጠቃላይ ፕሮጀክቱ 640 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚጠይቅ ሲሆን፣ እስካሁንም በምዕመናንና በበጎ አድራጊዎች ድጋፍ 135 ሚሊዮን ብር ወይም የጠቅላላ ግንባታውን 20 በመቶ የሚሆነውን ሥራ ማከናወን ተችሏል።

ይህ ዘመናዊ ሕንፃ ሲጠናቀቅ፤ ሰፊ የክርስትና ማጥመቂያ አዳራሽ፣ ለሠርግና ለተለያዩ ጉባኤዎች የሚውሉ አዳራሾች፣ እንዲሁም የገዳሙ አባቶች ማረፊያና ልዩ ልዩ ጽሕፈት ቤቶችን በማካተት አገልግሎቱን ምቹ እንደሚያደርገው ተገልጿል።

ይህንን ታላቅ መንፈሳዊና ታሪካዊ ፕሮጀክት ዳር ለማድረስም፣ ገዳሙ ከመጪው መጋቢት 11 እስከ መጋቢት 13 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በየቀኑ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ በሚዲያ ቀጥታ ስርጭት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ-ግብር አዘጋጅቷል።

በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚገኙ ምዕመናንና ለበጎ ተግባር ተነሳሽ የሆኑ ወገኖች፤ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በአቢሲኒያ እና በአዋሽ ባንክ በገዳሙ ስም በተከፈቱ ሒሳቦች ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።

እንዲሁም በስልክ ቁጥሮች በመደወልና ቃል በመግባት ለዚህ ታሪካዊ ሥራ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ተጠይቋል።

ገዳሙ ግንባታውን በሚቀጥለው የ2019 ዓ.ም አጠናቆ ለምዕመናን አገልግሎት ክፍት ለማድረግ ዕቅድ የያዘ ሲሆን፣ ለዚህም የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ትብብር በአክብሮት ጠይቋል።

ልዑል ወልዴ

መጋቢት 02/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *