የክስ ሂደቶች እየተበራከቱ በመምጣታቸው አሜሪካ ለሶማሌ ስደተኞች የምትሰጠውን ልዩ ጥበቃ ልታቆም ነው

የትራምፕ አስተዳደር በሚቀጥለው ሳምንት ለሶማሊያውያን የሚሰጠውን ጊዜያዊ የጥበቃ ፕሮግራም ለማቆም ተዘጋጅቷል፡፡

ይህ እርምጃ ወደ 1 ሺህ 1መቶ የሚጠጉ ሰዎች በአሜሪካ የመኖርና የመሥራት ሕጋዊ መብታቸውን እንዲያጡ ያደርጋል።

አራት የሶማሊያ ዜጎች እና ሁለት የስደተኞች መብት ተሟጋች ድርጅቶች ውሳኔው ሕገ-ወጥ ነው በማለት እና ውሳኔው የተላለፈበትን መንገድ በመቃወም ክስ መስርተዋል።

በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው ‹‹ሙስሊም አድቮኬትስ›› የተባለው የሕግ ተሟጋች ቡድን ለሶማሌ ስደተኞች የሚደረገውን ጥበቃ ማቆም በስደት ፖሊሲ የተሸሸገ ‹‹ዘረኝነት››ነው ብሎታል።

ከሳሾቹ እርምጃው በመንግስት ኃይሎች እና በአል-ሸባብ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ በቀጠለባት ሶማሊያ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ግምት ውስጥ ካላስገባ አድልዎ የመነጨ በመሆኑ ሕገ-መንግስታዊ አይደለም ሲሉ ይከራከራሉ።

በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ለአፍሪካውያን ስደተኞች የሚሟገተው ትልቁ ድርጅት ‹‹አፍሪካን ኮሚኒቲስ ቱጌዘር›› በካሜሩን፣ በኢትዮጵያ እና በደቡብ ሱዳን ዜጎች ስም በአጠቃላይ ወደ 12 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ጊዜያዊ ጥበቃቸውን ሊያጡ ስለሚችሉ የተለየ የሕግ ክስ እየመሰረተ ይገኛል።

የአሜሪካ የኢሚግሬሽን አስከባሪዎች በሚኒሶታ እና በሜይን የሚገኙ ሶማሌ ስደተኞችን ኢላማ እያደረጉ ሲሆን፤ ይህም በመላ አገሪቱ ቁጣንና ተቃውሞን ቀስቅሷል።

በሚኒሶታ ውስጥ ለግብር ከፋዮች ከ200 ሚሊየን ዶላር በላይ ኪሳራ አድርሰዋል በተባሉ ተደራራቢ የማህበራዊ አገልግሎት ማጭበርበር ወንጀሎች በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ተከሰዋል።

ዓቃብያነ ሕግ አብዛኛዎቹ ተከሳሾች የሶማሌ ተወላጆች መሆናቸውን ገልጸዉ፤እስካሁን 66 ያህል ሰዎች ጥፋተኛ መባላቸዉን አስታዉቀዋል፡፡

እስከዳር ግርማ

መጋቢት 03/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *